አሰላሳዩ፣ ሶሻሊስቱ፣ አብዮተኛው፣ ተመራማሪውና ፈላስፋው ፕሮፌሰር

8 Days Ago 371
አሰላሳዩ፣ ሶሻሊስቱ፣ አብዮተኛው፣ ተመራማሪውና ፈላስፋው ፕሮፌሰር

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፣ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ፖለቲካ ምሁር፣ ጠያቂ፣ ተመራማሪ፣ ፈላስፋ፣ መምህርና አሰላሳይ የነበሩት ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ብዙዎች እንደሚናገሩት ጎበዝ መምህር የነበሩ፣ ጨዋታ አዋቂ፣ ፒትልስ ሹራብ አዘውትረው ለባሽ፣ የጃዝ ሙዚቅ አፍቃሪ ነበሩ።

ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሽቴ በአራት ኪሎ ከ79 ዓመታት በፊት በ1937 ዓ.ም ነበር ከእናታቸው መንበረ ገብረማርያም እና አባታቸው እሸቴ ተሰማ የተወለዱት።

አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ጀምረው ኋላም በሀገረ አሜሪካ በሚገኙ ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎች ፍልስፍና ተምረዋል፤ አስተምረዋል፤ ተመራምረዋል።

በዊልያምስ ኮሌጅ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከየል ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ፕሮፌሰር አንድርያስ፣ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመልሰው በመምህርነት እንዲሁም በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።

ፕሮፌሰር አንድርያስ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፣ ብራውን፣ ዩሲኤልኤ፣ በርክሌይ እና ፔንሲልቬንያ ዩኒቨርስቲዎች ያስተማሩ ሲሆን በዩኔስኮ የሰብአዊ መብት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ሊቀ-መንበር በመሆን ሰርተዋል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ በሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ውስጥ በአባልነት በመሳተፍ በሙያቸው ያገለገሉት ፕሮፌሰር አንድርያስ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንትነታቸው ከለቀቁ በኋላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።

እኝህ ሙሁር ለእንስሳት ባላቸው ቅርበትና ፍቅር የሚታወቁ ሲሆን፤ ቤተኛ የሆነ አህያ እንደነበራቸውም ይነገራል። ፕሮፌሰሩ ይህንን አህያ ያገኙት መንገድ ላይ ተጥሎ ነበር።

ፕሮፌሰሩ ከባላባት ቤተሰብ ይገኙ እንጂ ለታችኛው ማህበረሰብ የተለየ ፍቅርና ሃሳብ ነበራቸው፡፡

አህያንም የገበሬው አገልጋይ ነው ብለው ያስባሉ። ለዛም ነው መንገድ ላይ ተጥሎ ያገኙትን አህያ ወደ ቤታቸው ወስደው እንደማንኛውም እንስሳ እየተንከባከቡ ሲያኖሩት የነበረው።

ሌላኛው የፕሮፌሰሩ አስገራሚ ታሪክ ሉሉ የተባለቸው ውሻ ነች፡፡ ሉሉ የፕሮፌሰሩ ተወዳጅ ውሻ ስትሆን ነገር ግን በጃንሆይ ተነጥቀዋታል።

ፕሮፌሰር አንድርያስ በልጅነታቸው አንዲት ሀንጋሪያዊት ለፕሮፌሰሩ ውሻ በስጦታ ትሰጣቸዋለች።

ታዲያ በአንዱ ቀን ታዳጊው እንድሪያስ ውሻቸውን ይዘው በአራት ኪሎ በኩል ወክ ለማድረግ ከቤት ይወጣሉ። በዛ በኩል ሲያልፉ የነበሩ የክቡር ዘበኛ አባላትም ውሻዋንና ታዳጊውን ተመልክተው ለማለፍ አልወደዱም መኪናቸውን አቁመው ከእንድሪያስ ላይ ሉሉን ቀምተው ወደ ቤተ መንግስት ወሰዷት።

በልጅነት ልባቸው የተቀበሏት ስጦታቸው በክቡር ዘበኞች የተወሰደችባቸው ፕሮፌሰር እንድሪያስ አምርረው አለቀሱ እረበሹ።

በዚህም የተነሳ ጃንሆይ የእንድሪያስን አጎት አስጠርተው በሉሉ ፈንታ መሬት እንስጥ እስከማለት ደርሰው ነበር።

ፕሮፌሰሩ በአንድ ወቅት ከፋና ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት ብዙዎች  በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ውጭ ሀገር ሂደው የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ሲያገኙ ለምን አፄ ሀይለስላሴን ትቃወማላችሁ? እዚህ ድረስ ልከው እያስተማራችሁ ብለው ይጠይቁና እኔን ሲያዩ እሱስ ቢቃወም ውሻውን ተቀምቶ ነው ብለው ይቀልዱ እንደነበረ ተናግረዋል።

በአንድ ወቅትም የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካሪያቸው ለነበሩት ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ እኛ ያለምክንያት ነው አራት ኪሎ የገባነው አንተስ ምክንያት አለህ ቢያንስ ውሻህ ቤተመንግስት ተቀብራለች እያሉ ቀልዶችን ያነሱ እንደነበረ አስታውሰዋል።

የፕሮፌሰር እንድሪያስ የቀድሞ ውሻ በኋላም የጃንሆይ ውሻ የሆነችው ሉሉ ብዙ ሀገራትን ከጃንሆይ ጋር በመዞሯ የተነሳ የፕሮፌሰሩ ጓደኞች ፕሮፌሰሩን እየጠሩ ሉሉ እንኳን አውሮፓና አሜሪካ ሂዳ መጣች አንተ እዚ ቁጭ ብለህ በማለት ይቀልዱባቸው እንደነበረ ፕሮፌሰሩ በትዝታ አንስተው ተናግረው ነበር።

መምህሩ እና ተመራማሪው ፕሮፌሰር አንድርያስ በሞራል እና ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች እንዲሁም ሥነ-ምግባር ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ለሕትመት አብቅተዋል።

የአንድ ልጅ አባት የሆኑት ፕሮፌሰር አንድርያስ፣ ሌሎች ሁለት ልጆችንም እንደ አባት ተንከባክበው ማሳደጋቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ በተወለዱ በ79 አመታቸው ነሐኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት የተለዩ ሲሆን ሥርዓተ-ቀብራቸውም ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል።

በናርዶስ አዳነ

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top