በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎችን ለመለየት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

1 Mon Ago
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎችን ለመለየት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ለሀገራዊ ምክክሩ የተሳታፊ ልየታ ባልተጀመረባቸው የአማራ እና የትግራይ ክልሎች፤ ልየታውን ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ገለጹ።
 
ከኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ጋይ ቆይታ ያደረጉት ቃል አቀባዩ፤ በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ሁሉንም አካላት በማረባረብ ለመስራት ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
 
እስካሁን ባለው ሂደት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ኮሚሽኑ ምንም አይነት የተሳታፊ ልየታ ስራ አለመጀመሩን ተናግረዋል።
 
በአማራ ክልል አሁን ላይ ያለው የጸጥታ ችግር እና ወቅታዊ ሁኔታ ኮሚሽኑ ስራውን እንዳይሰራ እንቅፋት እንደሆነበት ነው ቃል አቀባዩ የገለጹት።
 
ምንም እንኳን በክልሉ የጸጥታ ችግር ቢኖርም፤ ኮሚሽኑ በቀጣይ መሰራት ያለባቸውን ተግባራት ለመፈጸም አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጀመሩን ጠቅሰዋል።
 
በዚህም ክልሉ አንጻራዊ ሰላም ለማምጣት ከባለድርሻ አካላት እና በግጭት ውስጥ ካሉ ወገኖች ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
 
በተመሳሳይ በትግራይ ክልል የተሳታፊ ልየታ አለመጀመሩን ያነሱት አቶ ጥበቡ፤ ኮሚሽኑ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተድደር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በሌላ በኩል የተሳታፊ ልየታው በተጠናቀቀባቸው በከተማ አስተዳደር እና በክልል ደረጃ የሚወከሉ ተወካዩችን፤ ከተቋማት እና ከማህበራት ተወካዮችን የማቀናጀት እና የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ተሳታፊዎች የሚለዩት በሁለት ደረጃ መሆኑን ያነሱት አቶ ጥበቡ፤ ለምክክሩ የአጀንዳ ሀሳብን የሚሰጡ ተወካዮች የሚመረጡበት የመጀመሪያው ደረጃ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሁለተኛው ደግሞ የአጀንዳ ሀሳብ የሚሰጡ ተወካዮች የሚለዩበት መሆኑን ነው የገለጹት።
 
ሀገራዊ ምክክሩ፤ ሀገሪቷ ላለችብት ወቅታዊ ሁኔታ እና ለዘመናት ሲንከባለሉ ለመጡ ችግሮች ከአዙሪት ለመውጣት ሁነኛ አማራጭ መሆኑን በመገንዘብ፤ ሁሉም ህብረተሰብ ለምክክሩ መሳካት በቁርጠኝነት እንዲሰራ ቃል አቀባዩ ጠይቀዋል።
 
በተስሊም ሙሀመድ
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top