እ.አ.አ ጥቅምት 7 ቀን 2023 የእስራኤልን ድንበር ጥሶ በመግባት ጥቃት የፈፀመው የሐማስ ሻቲ ባታሊዮን መሪ ኮማንደር ሃይታም ኩዋጃሪ በአየር በተፈፀመት ጥቃት መገደሉን የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ ዳኒኤል ሐጋሪ ገለጹ።
ቃል አቀባዩ እሑድ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ኩዋጃሪ ከጋዛ ወጣ ብሎ በሚገኝ አል-ሻቲ በተባለ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ቅጥር ግቢ ውስጥ በተፈፀመበት ጥቃት መገደሉን አስታውቀዋል።
የእስራኤል ሠራዊት በሰጠው መግለጫ፣ አል-ሻቲ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ላይ የሚወስደውን ጥቃት አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ስፍራውን የሚቆጣጠሩ እያንዳንዱን የሐማስ ኮማንደሮች እንደሚያጠፋ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል ጋዛ ላይ በፈፀመችው ጥቃት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከ700 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አንድ የሀገሪቱ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ዋና ዳይሬክተር ለአልጀዚራ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከሰሜናዊ ጋዛ የተፈናቀሉ ከ10 ሺህ በላይ ፍልጤማውያን ስደተኞች የሚገኙት ከማል አድዋል ሆስፒታል ላይ ምሽቱን በደረሰ የአየር ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸው እና ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጿል።
ከእሑድ ጠዋት ጀምሮ ቢያንስ 99 አስከሬኖች ወደ ሆስፒታሉ መወሰዳቸውንም ምንጮች ገልጸዋል።
እስራኤል ጋዛ ላይ ከሁለት ወራት በፊት የከፈተችውን ጥቃት ተከትሎ እስካሁን 1.8 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች መፈናቀላቸውም ተገልጿል።