በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች መጀመራቸው ተገለጸ

1 Yr Ago 935
በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች መጀመራቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ (ቻርጅ) የሚያርጉበት ጣቢያዎች ገንብቶ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያችሉ መሰረተ ልማቶችን ለማከናወን የሚስችል የስራ ማስጀመሪያ መርሐግብር ዛሬ ተካሄዷል።

በመርሐግብሩ ላይ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዜጎች በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሸከርካሪዎችን የመጠቀም ልምድ እየጎለበተ መጥቷል ብለዋል።

መኪኖቹን ለመጠቀም ያለው ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ አሽከርካሪዎች ለተሽከርካሪያቸው ኃይል የሚሞሉበት መሰረተ ልማት ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ይህንንም ለማድረግ ተቋሙ ከካርዲናል ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመሆን የኤሌክሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ለመገንባት ስምምነት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ በበኩላቸው በመዲናዋ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ አሽከርካሪዎች ቻርጅ የሚያደርጉበት ጣቢያ ግንባታ አበረታች ጅማሬ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩም በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ በኢትዮጵያ የተጀመረው ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት ስራ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በርኦ ሃሰን በበኩላቸው በኤሌትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሸከርካሪዎችን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የባለሀብቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ በመዲናዋ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሸከርካሪዎች ኃይል የሚሞሉበት ጣቢያ ለመገንባት ለሚደረገው እንቅስቃሴ የቅርብ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

የካርዲናል ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሊሊያ ኃይሉ በመዲናዋ 500 የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ወደ ስራ ለማስገባት መታቀዱን ጠቁመዋል።

አሁን በአዲስ አበባ የተጀመረው ፕሮጀክት ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋት እቅድ መኖሩንም አመልክተዋል።

በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ 4 ሺህ 800 በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አውቶቢሶች እና 148 ሺህ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ መታቀዱ በመርሐግብሩ ማስጀመሪያ ወቅት ተገልጿል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top