የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‘ኢትዮ ዳይሬክት’ የተሰኘ ዲጂታል የውጭ ምንዛሬ መላኪያ አገልግሎት ይፋ አደረገ

1 Yr Ago
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‘ኢትዮ ዳይሬክት’ የተሰኘ ዲጂታል የውጭ ምንዛሬ መላኪያ አገልግሎት ይፋ አደረገ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‘ኢትዮ ዳይሬክት’ (EthioDirect) የተሰኘ ዲጂታል የውጭ ምንዛሬ መላኪያ አገልግሎት ጥቅም ላይ ማዋሉን አስታወቀ።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ አገልግሎቱን በይፋ ሥራ ለማስጀመር በተዘጋጀ መርሐ-ግብር ላይ እንዳሉት፣ ወቅቱን ያገናዘበ ዲጂታል የገንዘብ መላኪያ ዘዴን ተግባራዊ ለማድረግ ፕላትፎርሙ ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል።
መተግበሪያው ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ መሆኑን የተናገሩት አቶ አቤ፣ ደንበኞች ምቾታቸው እንደተጠበቀ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ከክፍያ ነፃ ሐዋላ መላክ የሚችሉበት ዘመናዊ አገልግሎት መስጫ መሆኑን አስረድተዋል።
ደንበኞች እንደ ማስተርካርድ እና ቪዛ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶችን በመጠቀም በመተግበሪያው ገንዘብ መላክ የሚችሉ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሚላከው ገንዘብ በቀጥታ ወደ ተቀባዩ የባንክ ሒሳብ የሚገባ ሲሆን በቀጣይ ወደ ሲቢኢ ብር ዋሌት ማስገባት ወይም ተቀባዩ በአቅራቢያው ከሚገኝ የባንክ ቅርንጫፍ እንዲቀበል ለማስቻል ይሠራል ማለታቸውን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
ደንበኞች ‘EthioDirect’ መተግበሪያን ከፕሌይ ስቶር እና አፕስቶር በማውረድ እና ሞባይል ስልካቸው ላይ በመጫን ከውጪ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ ገንዘብ መላክ እንደሚችሉ የተገለፀ ሲሆን፣ በቀጣይ በhttps://www.ethiodirect.com ድረ ገጽ አገልግሎቱ እንደሚቀርብ ታውቋል።
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top