የአፄ ፋሲል አብያተ መንግሥታት እድሳት የትውልድ ቅብብሎሽ የታየበት ድንቅ ቅርስ ነው፡- የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

23 Hrs Ago 96
የአፄ ፋሲል አብያተ መንግሥታት እድሳት የትውልድ ቅብብሎሽ የታየበት ድንቅ ቅርስ ነው፡- የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ
የፋሲል አብያተ መንግሥታት እድሳት የትውልድ ቅብብሎሽ የታየበት፣ አንድነት የተገነባበት ድንቅ ቅርስ መሆኑን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
 
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ እየተገነቡ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
 
በጉብኝቱ በርካታ ዓመታት ታሪክ ያለው አስደናቂ የኪነ ሕንጻ ግንባታ አይተናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ አባቶቻችን አሻራቸውን አስቀምጠው የይቻላል መንፈስን ለትውልዱ አስተምረውናል ብለዋል።
 
አብያተ መንግሥታቱ ለበርካታ ዓመታት ተዘንግቶ ወደ መፍረስ ተቃርቦ ነበር፤ ዛሬ ላይ የሚመጥነውን እድሳት አግኝቷል ብለዋል። በዚህም የራሳችንን ታሪክ በራሳችን መጠበቅና መንከባከብ እንደምንችል ያሳየንበት ነው ሲሉ አክለዋል።
 
በከተማዋ የተሠራው የኮሪደር ልማት ለቅርሱ ድንቅ ውበት መሆኑን ገልጸው፤ ከተማዋን የሚመጥናት ግንባታ በመከናወኑ ጎንደር ውበቷ እንዲታደስ ሆኗል ብለዋል።
 
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች በሚመች ሁኔታ መከናወኑን መመልከታቸውንም አክለዋል ገልጸዋል።
 
የጎንደር - አዘዞ አስፓልት መንገድ የኅብረተሰቡ የዓመታት ጥያቄ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ አሁን ላይ ወደ መጠናቀቁ ደረጃ እየደረሰ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
 
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስት የቅርስ እድሳት ሁለተኛው ምዕራፍ መጀመሩን ገልጸዋል።
 
የእድሳት ስራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተገኙ ልምዶች ለሁለተኛው እና ለሶስተኛ ምዕራፍ በተሻለ መንገድ ለማከናወን እድል የሚፈጥር መሆኑን መናገራቸውን የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽ መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top