የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች ለህብረተሰቡ ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡-ኮርፖሬሽኑ

1 Mon Ago 173
የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች ለህብረተሰቡ ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡-ኮርፖሬሽኑ

የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን በመከታተል ለህብረተሰቡ ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ገልጿል።

በአዲስ አበባ የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች የህዝብ መዝናኛ ቦታዎችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፤ ኮርፖሬሽኑ እየለሙ ካሉ ፓርኮች ውስጥ 27 የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን መረከቡን ተናግረዋል።

በመንግስትና በተለያዩ ተቋማት አማካኝነት የለሙ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን ተረክቦ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ፣ የማልማትና ነባሮቹንም የማደስ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች ለህብረተሰቡ መዝናኛነት፣ ለቱሪስት መስህብነትና ለስራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ነጻነት ዳባ ጠቅሰዋል።

በዘርፉ የግሉን ሴክተር ለማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ በግማሽ ዓመቱ በኮሪደር ልማት የተገነቡ የህዝብ መዝናኛዎችን ሳይጨምር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የህዝብ መዝናኛ ፓርኮችን መጎብኘታቸውንም ተናግረዋል።

በኮርፖሬሽኑ ስር የሚገኙ የህዝብ መዝናኛ ፓርኮች አገልግሎት በአብዛኛው በነጻ መሆኑን የገለጹት ስራ አስፈጻሚዋ፤ በውስን ፓርኮች ላይ ለተለያዩ አገልግሎቶች መሸፈኛ ሲባል አነስተኛ ገቢ እንደሚሰበሰብ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም በግማሽ ዓመቱ 60 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉንና ከአምስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top