በአማራ ክልል በ2016/17 የምርት ዘመን እስከ አሁን ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በክልሉ በምርት ዘመኑ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ ሰብሎች ማልማት ተችሏል።
ከለማው ሰብል ውስጥ እስከ አሁን ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ሰብል መሰብሰቡን ነው የተናገሩት።
የምርት ብክነትን በመቀነስ የደረሱ ሰብሎች በወቅቱ እንዲሰበሰቡ ለማድረግ በ51 ኮምባይነር እና 487 አነስተኛ የሰብል መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ምርቱ እንዲሰበሰብ መደረጉም ተገልጿል።
በአጨዳ፣ በማጓጓዝ፣ በክመራ እና በውቂያ ወቅት ሊደርስ የሚችለውን የምርት ብክነት ለመቀነስ የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል።