በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ እየተከበረ የሚገኘው 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ሲምፖዚየም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር ባደረጉት ንንግር፤ ግጭቶችን በዘላቂነት በመከላከል በክልሎች መካከል ያለውን መስተጋብር ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የተገኙ ህገ-መንግስታዊ ድሎችን ለማስቀጠል፣ ሰላም ለማስፈን፣ ፍትህ እንዳይዛባ፣ የዜጎች የመዘዋወር እና የመስራት መብት እንዲጠበቅ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሀገረ መንግሥት ግንባታው ሂደት በየዘመኑ ሲጀመር ሲፈርስ፣ ሲወድቅ ሲነሳ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን የተጀመረው የሀገረ መንግሥት ግንባታ በስኬት እንዲጓዝ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ በበኩላቸው፤ የ19ኛው ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መከበሩ በክልሉ በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት ለተቀሩት አከባቢዎች ለማሳየት ፋይደው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
አፈ ጉባኤዋ የብሔር ብሄረሰቦች ቀን በዓል የኢትዮጵያ ሕዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነዉ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የፀደቀበትን ቀንን በማሰብ የሚከበር መሆኑንም ገልፀዋል።
ሲምፖዚየሙ በጋሞ ባህልና ምርምር ማዕከል አዳራሽ እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን፤ በመድረኩም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በአፎሚያ ክበበው እና በትዕግስቱ ቡቼ