በሐረሪ ክልል የህፃናት መጠነ መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ

17 Days Ago 126
በሐረሪ ክልል የህፃናት መጠነ መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ
በሐረሪ ክልል የህፃናት መጠነ መቀንጨርን ዜሮ በማድረግ ጤናማ እና አምራች የሰው ኃይልን ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
 
በሐረሪ ክልል የተቋቋመው የሥርዓተ ምግብ እና ኒውትሪሽን ምክር ቤት ማብሰሪያ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተካሄደ ነው።
 
መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት ርዕስ ምተዳድሩ በክልሉ አካላዊ እና አዕምሮ ዕድገቱ የዳበረ ጤናማ ትውልድን መገንባት ትኩረት እንደተሰተው ገልጸዋል።
 
ለበርካታ የአፍሪካ አገራት ፈተና የሆነው የህፃናት መጠነ መቀንጨር በልጆች ጤና ብቻ ሳይሆን በአዕምሮ ዕድገት ላይ ተፅኖ እያሳደረ የሚገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
 
የሰቆጣ ቃልኪዳን መርሀ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ የመቀንጨር ችግርን በአንፃራዊነት መቀነስ መቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
በክልሉ የማህበረሰቡን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
 
ኢትዮጵያ ያላትን የሰው ሀይል አልምቶ መጠቀም እንደሚገባ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ የሥርዓተ ምግብ ችግርን ከመቅረፍ ጀምሮ ትውልዱ ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በማስቻል መጠነ መቀንጨርና መቀጨጭን ዜሮ ለማድረግ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
 
በተለይ የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና ምርታማነትን በማጎልበት የማህበረሰቡን የስርዓ ምግብ ማስተካከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የትምህርት ቤቶች ምግባም የስርዓተ ምግብ ችግሩን ለመቅረፍ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አክለዋል።
 
አንድ ህፃን ከማህፀን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ የተስተካከለ ስርዓተ ምግብ እንዲኖረው በማድረግ መቀንጨርን ማጥፋት የሚቻል መሆኑን አስገንዝበው፤ ክልሉ ንቅናቄውን ውጤታማ ለማድረግ የአቻ በጀት በመመደብ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
 
በክልሉ የማህበረሰቡን የስርዓተ ምግብ በማስተካከል አንፃራዊ መሻሻሎች ቢኖሩም የማህበረሰቡን የአመጋገብ ባህል በማሳደግ የመጠነ መቀንጨር ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
 
በክልሉ የአቅርቦት ሳይሆን የስርዓተ ምግብ ግንዛቤ እጥረት መኖሩን የመጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የስርዓተ ምግብን የተመለከቱ ግንዛቤዎችን ለማህበረሰቡ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
 
በስርዓተ ምግብ ችግር ምክንያት የሚከሰተዉን መቀንጨርና መቀጨጭን ዜሮ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ስራውን በባለቤትነት እንዲመሩት ርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top