የኢትዮ-ጅቡቲ ግንኙነት ከጋራ ድንበር አስተዳደር ባለፈ በደም የተሳሰረ ነው - ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት

1 Mon Ago 183
የኢትዮ-ጅቡቲ ግንኙነት ከጋራ ድንበር አስተዳደር ባለፈ በደም የተሳሰረ ነው - ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት

የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ግንኙነት ከጋራ ድንበር አስተዳደር ባለፈ በደም የተሳሰረ መሆኑን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ፡፡

28ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የድንበር አስተዳዳሪዎች እና ኮሚሽነሮች የጋራ ስብሰባ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በቢሾፍቱ መካሄድ ጀመሯል፡፡

የጋራ ስብሰባው ልዑክ መሪ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፤ የኢትዮ-ጅቡቲ ግንኙነት ከጋራ ድንበር አስተዳደር ባለፈ በደም የተሳሰረ መሆኑን ተናግረዋል።

ሃገራቱ ያላቸው የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ደህንነትን የማስከበር የጋራ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አውስተዋል።

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በኢጋድ ማዕቀፍ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ጉልህ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ አገራት በተለያዩ ዘርፎች በኤሌክትሪክ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ እና በንግድ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ጠንካራ ግንኘነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ጸሃፊ ሱሉማን ሙአሚን በበኩላቸው፤ የኢትዮ ጅቡቲን መልካም ግንኙነት ወደፊት ለማስቀጠል በጋራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ በድንበር ጉዳዮች ላይ በተለይም የጋራ መሰረተ ልማትን በትብብር በማጠናከር የጋራ ራዕያችንን እንደምናሳካ አልጠራጠርም ብለዋል፡፡

ዋና ጸሃፊው የሀገራቱ ግብ እና ራዕይ ተመሳሳይ በመሆኑ በሰላም እና ደህንነት  በጋራ በመሆን ልማታችንን በማሳደግ ተጠቃሚነታችንን እናረጋግጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የውይይት መድረኩ የድንበር አስተዳደር፣ የንግድ ግንኙነት እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር ላይ ትኩረቱን አድርጎ ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው።

በስብሰባው በሁለቱ አገራት የመከላከያ፤ የንግድ የፀጥታ እና ደህንነት ፖሊስ የኢሚግሬሽን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ  አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዩሃንስ ፍስሃ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top