የባላንዶር ሽልማት ውዝግብ እንደቀጠለ ነው

1 Mon Ago 418
የባላንዶር ሽልማት ውዝግብ እንደቀጠለ ነው

በየዓመቱ በእግር ኳስ ስኬታማ ለሆኑ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ክለቦች የሚሰጠው የምድራችን ትልቁ ሽልማት ባላንዶር ትላንት ምሽት በፈረንሳይ መዲና ተካሂዷል፡፡

በወንዶቹ የማንችስተር ሲቲው ሮድሪ የክብሩ ባለቤት ሲሆን፣ የሪያል ማድሪዱ ቪኒሺየስ ጁኒየር እና የቡድን አጋሩ ጁድ ቤሊንግሃም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሆነዋል፡፡ የባርሴሎናዋ ቦንሜቲ የሴቶችን ሽልማት ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ አሸንፋለች፡፡

በወንዶች ክለብ ሪያል ማድሪድ ምርጥ ክለብ የተባለ ሲሆን፣ በሴቶች ደግሞ የባርሴሎና ክለብ ምርጥ ተብሎ ተሸልሟል፡፡ ሪያል ማድሪድ በሁለት ዘርፍ ማለትም በምርጥ አሰልጣኝ እና ምርጥ ክለብ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ቀድሞ ሽልማቱን ያሸንፋል ተብሎ የተጠበቀው እና በእርግጠኝነትም የተወራለት ቪኒሺየስ ጁኒየር አለማሸነፉን የሾለከ መረጃ ደርሶኛል ያለው ሪያል ማድሪድ ልዑካኑን ወደ ቦታው ሳይልክ ቀርቷል፡፡

በውድድር ዓመቱ ከሪያል ማድሪድ ጋር የላሊጋ እና የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያሸነፈው ቪኒሺየስ ጁኒየር በብዙዎች ግምት ሽልማቱን ማሸነፍ እንደሚችል ታስቦ ነበር፡፡

ምንም እንኳን ቪኒሺየስ ጁኒየር እና ጁድ ቤሊንግሃም ሁለተኛ እና ሶስተኛ፣ ዳኒ ካርቫሃል ደግሞ አራተኛ ሆነው ቢያጠናቅቁም ክለባቸው ሪያል ማድሪድ ግን ሽልማቱ ለቪኒሺየስ ይገባው ነበር ብሎ በማመኑ ደስተኛ እንዳልሆነ ከዝግጅቱ ቦታ በመቅረት ገልጿል፡፡

ሽልማቱን እንደሚያሸንፍ የተገመተው ቪኒሺየስ ጁኒየር ውጤቱ ከወጣ በኋላ በ "X" ገጹ በለጠፈው መልዕክት “እኔ ካስፈለገ አስር ጊዜ ማድረግ እችላለሁ፤ እነሱ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አይደሉም” በማለት ቅሬታውን ገልጿል፡፡

ሽልማቱ እንዳይሰጠው የተደረገው ዘረኝነትን በመቃወሙ እንደሆነ ገልጾ፣ በእግር ኳሱ ውስጥ የሰፈነውን ዘረኝነት መፋለሙን እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡

የሪያል ማድሪድ አመራሮችም ቪኒሺየስ ለምን እንደዚህ እንዳለ ተጠይቀው፣ "የእግር ኳሱ አመራር በስፖርቱ የሰፈነውን ዘረኝነት የሚቃወሙ ተጨዋቾችን ስለማይፈልግ ነው" በማለት ነው ገልጸዋል፡፡

ብራዚላዊቷ የሴቶች እግር ኳስ ኮከብ ማርታ በበኩሏ፣ "ቪኒሺየስ የዓለም ምርጥ ተጫዋች ምርጫን እንደሚያሸንፍ ዓመቱን በሙሉ ጠብቄ ነበር፤ አሁን ባላዶንር ለእርሱእንደማይገባ ነገሩን" በማለት በኢንስታግራም ገጿ ላይ በለቀቀችው ቪዲዮ ንዴቷን ገልጻለች።

የቪኒሽየስ ጁኒየር የቡድን አጋር የሆነው እና "የእግር ኳስ ፖለቲካ" በማለት ሥነ-ሥርዓቱን የገለጸው ኤድዋርዶ ካማቪንጋ በበኩሉ "ወንድሜ አንተ ምንም ዓይነት ሽልማት ዋጋህን የማይመጥንህ የዓለማችን ምርጡ ተጨዋች ነህ" በማለት አጋርነቱ ገልጾለታል፡፡

በላሉ ኢታላ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top