ዘላቂ ሰላም፣ኢኮኖሚ እና የመንግስት አገልግሎትን ማዘመን የምክር ቤቱ ዋነኛ ትኩረቶች ናቸው፡- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

2 Mons Ago 440
ዘላቂ ሰላም፣ኢኮኖሚ እና የመንግስት አገልግሎትን ማዘመን የምክር ቤቱ ዋነኛ ትኩረቶች ናቸው፡- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን የአንድ ዓመት የሥራ ጊዜው አድርጎ የደነገገው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ፈጣን የሆነውን የኢኮኖሚ እድገትን ማስቀጠል እና የመንግስት አገልግሎትን ማዘመን የ2017 የስራ ዘመን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎቹ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
 
የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ለዘላቂ ሰላም ማጣት የሚነሱ ቅሬታዎች እንዲፈቱ ከበጀት ማፅደቅ ጀምሮ ያሉ ስራዎች ፍትሃዊ እና ሁሉን አካታች አንዲሆኑ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ይህንንም ሊያጠናክሩ የሚችሉ የሕግ ማሻሻያዎችን ማድረግ እና ተግባራዊነታቸውን የመከታተል ስራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
 
በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የ2016 በጀት ዓመት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሆነው ተቀምጠው የነበሩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ልየታ ስራዎች፣የሽግግር ፍትሕ ተፈፃሚነት እና የፍትሕ ተቋማት ሪፎርም ሲሆን ይህም ውጤታማ በሆነ መልኩ መተግበሩን ነው የገለጹት፡፡
 
የፌደራሉ መንግስት ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው ምክር ቤቱ፤ በአንቀፅ 55 ስር ባሉት 19 ንዑስ አንቀፆች በተሰጠው ስልጣን መሰረት ባለፈው ዓመት ሕግ የማውጣት፣አስፈፃሚ አካላት ላይ ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ እንዲሁም የህዝብ ውክልና ስራዎችን የመስራት ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣቱን አንስተዋል፡፡
 
በዚህም 46 አዋጆች፣ 2 ደንብ ያወጣ ሲሆን 12 ወደ 2017 በጀት ዓመት የተሸጋገሩ የሕግ ማዕቀፎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
 
አፈ-ጉባዔው በክትትል እና ቁጥጥር ሂደት ውስጥ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በሩብ ዓመቱ የተሰሩ ስራዎችን የሚገመግም መሆኑን አስታውሰው፤ ይህም ከተያዘው የ10 ዓመት እቅድ አኳያ ምን ያህል ተፈፃሚ ሆኗል የሚለው በሪፖርት ብሎም በመስክ ቅኝት እንደሚገመገም ገልጸዋል፡፡
 
ከዚህ ጋር በተያያዘ ያልተፈፀሙ እና እርምት የሚሹ ጉዳዩች ሲኖሩ የአስፈፃሚው የበላይ አካል የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማሳወቅ የአመራር መዋቅር ፍተሻ እና ማስተካከል በማድረግ እርምጃ የመውሰድ ስራዎች እንደሚተገበሩ ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ መሰል እርምጃ የኦዲት ሪፖርት ጉልህ ሚና እንዳለው አያይዘው አንስተዋል፡፡
 
የህዝብ ውክልና ስራን መስራት ኃላፊነቱ የሆነው ምክር ቤቱ፤ ወርሃ የካቲት እና የክረምቱ ወራት የመራጩን ህዝብ ጥያቄ የተቀበለበት እና የሚመለስበትን መንገድ የቃኘበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 
የተያዘው በጀት ዓመት በንግግር ችግሮቻችንን ፈተን ዘላቂ ሰላም የምናስፍንበት፣ፈጣኑ ኢኮኖሚያችን የኑሮ ውድነትን የሚያረጋጋበት፣የስራ አጥነትን የሚቀንስበት እንዲሁም በመንግስታዊ ተቋማት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ከታችኛው ቀበሌ ጀምሮ እንዲፈቱ የምንሰራበት ዓመት መሆኑን ማህበረሰቡ ሊያውቅ ይገባል ብለዋል፡፡
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top