ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የሜልበርን ኦሎምፒክ ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውለበለበ ባለ ታሪክ ነው፡፡
በብስክሌት ተወዳዳሪነት እና በአሰልጣኝነት ኢትዮጵያን ወክሎ በሦስት የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ ውስጥ ልዩ ስፍራ ያለው አትሌት ነው፡፡
በተወዳደረባቸው የተለያዩ መድረኮች 26 ዋንጫዎች እና 32 ሜዳልያዎች የተሸለመ ድንቅ ብስክሌተኛ አትሌት ገረመው ደምቦባ የተወለደው ታህሳስ 7 ቀን 1925 ዓ.ም በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ አካባቢ ነው።
ለሀገሩ ባደረገው አስተዋጽኦ የ4ኛው ኢቢሲ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የህይወት ዘመን ተሸላሚ በመሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ሽልማቱን ተቀብሏል።
የመጀመሪያ ደርጃ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (የአሁኑ ኮከበ ጽባሕ) ትምህረት ቤት የተማረው ገረመው፥ ገና የሰባት ዓመት ህጻን እያለ ብስክትሌት መንዳት መጀመሩን በተደረጉለት ቃለ መጠይቆች ተናግሯል።
ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ከሰፈሩ እስከ ኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ያለውን ርቀት ለመጓዝ ይጠቀምበት የነበረውን ብስክሌቱን በ30 ብር የገዙለት እናቱ ነበሩ፡፡ ይቺ ብስክሌትም እስከ ሜልቦርን ለዘለቀው የስፖርት ሕይወቱ መነሻ ሆነችው።
የመጀመሪያው የብስክሌት ውድድሩን በ1943 ዓ.ም በ18 ዓመቱ ያደረገው አትሌት ገረመው፣ ረጅም ልምድ ካካበቱ የጣሊያን እና ግሪክ ተወዳዳሪዎች ጋር ተፎካክሮ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ፡፡ ይህም ለቀጣይ ስኬቱ መንደርደሪያ ሆነለት።
በ1945 ዓ.ም በተደረገው የሀገር ውስጥ ውድድር አንደኛ የወጣው አትሌት ገረመው፣ ራሱን እያጠናከረ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ዕድልን መጠባበቅ ጀመረ፡፡
እ.አ.አ በ1924 ዓ.ም አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ለሥራ ጉብኝት ወደ ፈረንሳይ ይሄዳሉ፡፡ በወቅቱ ፈረንሳይ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን እያዘጋጀች ስለነበር የሚፈልጓቸውን ባለሥልጣናት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
የፈረንሳይ ባለሥልጣናትም የኦሎምፒክ መስተንግዶአቸውን ሲጨርሱ ሊያነጋግሩአቸው ቀጠሮ በመስጠት እግረ መንገድም አልጋ ወራሽ ተፈሪ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን እንዲመለከቱ ጋበዟቸው፡፡ ራስ ተፈሪም ኦሎምፒክን የተመለከቱ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆኑ፡፡
ጉብኝቱን አጠናቅቀው ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል እንድትሆን እና በኦሎምፒክ እንድትሳተፍ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ የኢትዮጵያ ጥያቄ ከአፍሪካ ብቸኛ በመሆኑ ይመስላል የራስ ተፈሪ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ለበርካታ ዓመታት ቆየ፡፡ ተስፋ ያልቆረጠችው ኢትዮጵያ ግን ጥያቄዋን ቀጥላ ከ32 ዓመታት በኋላ ምላሽ አገኘች፡፡ በ1956 የመጀመሪያ የኦሎምፒክ ተሳትፎዋን አንድ ብላ ጀመረች፡፡
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በቦታው ለመድረስ ሰባት ቀን እና ሌሊት ፈጀባቸው፤ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ የተደረገው በአውስራሊያዋ ሜልቦርን ሲሆን ጊዜውም 1956 ነበር፡፡
ከልዑካን ቡድኑ መካከል ደግሞ ብስክሌተኛው አትሌት ገረመው ደምቦባ ይገኝበታል፡፡ አትሌት ገረመው ስለ አድካሚው ጉዟቸው ሲያስታውስ "አሜሪካ ስሪት ዳኮታ የሚባል አሮጌ አውሮፕላን ተፈቀደልን፤ አውስትራሊያ ለመድረስ ሰባት ቀን ሰባት ሌሊት ፈጀ፤ ሰባት ቀን አየር ላይ ስንቆይ ምግብ የለ ደርቀን ሥጋ እና አጥንታችን ተጣብቆ ከጦር ምርኮኝነት የተለቀቅን ይመስል ነበር" ብሎ ነበር።
ኢትዮጵያ በሜልቦርን ኦሎምፒክ በአስር የውድድር ዓይነቶች በአስራ ሁለት አትሌቶች ተካፍላ የነበረ ሲሆን፣ በብስክሌት የተሳተፈው ገረመው ደምቦባ 24ኛ ደረጃን ይዞ የጨረሰበት ውጤት ኢትዮጵያን ከአፍሪካ እና ከእስያ ተፎካካሪዎች ቀዳሚ አድርጓታል።
ከገረመው በተጨማሪ መስፍን ተስፋዬ፣ ፀሐይ ባሕታ እና መንግስቱ ንጉሴ የነበሩበት የኢትዮጵያ የብስክሌት ቡድን ኢትዮጵያ በብስክሌት በቡድን አራተኛ እንድትወጣ አስችሏታል።
በ1960 የጣሊያኗ ሮም ኦሎምፒክ ላይ የተሳተፈው ገረመው፤ ከሜልቦርን ኦሎምፒክ ልምዱ በመነሳት እና ባደረገው ዝግጅት ምክንያት መልካም ውጤት ያመጣል ተብሎ ቢጠበቅም ውድድሩ ላይ እያለ በተሠራበት ጥፋት በመጎዳቱ ውድድሩን ሳይጨርስ ቀረ።
በፍጥነት ላይ እያለ ተንኮለኛ ተፎካካሪዎቹ የብስክሌቱን ጎማ ከኋላ ነክተው እንዲወድቅ አድርገውት ትከሻውና እግሩ ተሰበረ፤ በዚህ ምክንያትም በአየር አምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ሕክምና ተደረገለት። ያ አሳዛኝ አደጋም ከሚወደው የብስክሌት ስፖርት እስከመጨረሻው አራቀው፡፡
ገረመው ደምቦባ በራሱ ጋላቢነት በብስክሌት ውድድር መሳተፍ ባይችልም ፊቱን ወደ አሰልጣኝነት አዙሮ ብስክሌተኞችን ማፍራቱን ቀጠለ፡፡ በአሰልጣኝነቱም በ1968ቱ የቶክዮ ኦሎምፒክ የተሳተፈውን የብስክሌት ቡድን መርቶ ተሳትፏል፡፡ በ1973 በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው ሁለተኛ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የብስክሌት ቡድን ይዞ በመጓዝ የወርቅ ሜዳሊያ ይዞ ተመልሷል።
ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው የብስክሌት ተወዳዳሪዎች ሁሉ ስኬታማ እንደሆነ የሚነገርለት ገረመው ደምቦባ፣የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በ90 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ገረመው በሕይወት ባይኖርም የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ በታሰበ ቁጥርም አብሮ ይታሰባል፡፡