የውጭ ምንዛሬን በሚመለከት የግለሰቦች መብትና ግዴታ

1 Mon Ago 1837
የውጭ ምንዛሬን በሚመለከት የግለሰቦች መብትና ግዴታ

ከሕጎች መነሻ አንዱ ሕጉን የሚያወጣው ሀገር የሚከተለው ፖሊሲ ነው። ፖሊሲን በቀላል አገላለፅ ስናስቀምጠው አንድ ሀገር ወይም ተቋም በአንድ ጉዳይ ላይ የሚከተለውን መሰረታዊ አቅጣጫ እና አካሄድ ወይም የሚመራባቸውን ዋና ዋና መርሆች የሚገልፅ ሰነድ ነው ልንለው እንችላለን ።ሀገራት ፖሊሲያቸውን ሲለውጡ ብዙውን ጊዜ ነባሩን ፖሊሲ ለመተግበር እና ለማስፈፀም የወጡ ሕጎችንም አብረው ይቀይራሉ ወይም ያሻሽላሉ። እኛም ሀገር ከሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ግብይት እና አስተዳደር ፖሊሲን የቀየረ አዲስ ፖሊሲ ይፋ ተደርጎ እየተተገበረ ይገኛል። ይህን ተከትሎም ነባሩን የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ የሚተካው የውጭ ምንዛሪ መመሪያ ቁጥር FXD/01/2024 በሥራ ላይ ውሏል። በመሆኑም ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ እንደ ግለሰብ የሚመለከቱ መብት እና ግዴታዎቻችን በዚህ ፅሁፍ ላይ እንመለከታለን።

ብርን ከሀገር ማስወጣት ወይም ማስገባት

በቀድሞው መመሪያ ላይ እስከ ብር 10,000 (አስር ሺህ) ብቻ ነበር ወደ ጅቡቲ ይዞ መውጣት እና ከጅቡቲ ይዞ ወደ ኢትዮጽያ ግዛት መግባት የሚፈቀደው።

በአዲሱ መመሪያ የተጨመረ ነገር ቢኖር ይህ ፍቃድ ለጅቡቲ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የጎረቤት ሀገራት የወደብ ከተሞች ወደ ኢትዮጽያ ለመግባትና ወደ ሌሎች የጎረቤት ሀገራት የወደብ ከተሞችም እስከ አስር ሺ ብር ይዞ ለመውጣት መፈቀዱ ነው።

ከነኚህ ሀገራት ውጭ ካሉ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ለመግባትም ከኢትዮጵያ ይዞ ለመውጣት የሚፈቀደው የብር መጠን ግን ለአንድ ጉዞ ብር 3,000 (ሦስት ሺህ) ብቻ ነው።

ጉዞዎ እክል እንዳይገጥመው እና በወንጀል እንዳያስጠይቅዎ ከኢትዮጵያ ሲወጡም ሆነ ሲገቡ ሌሎች በሕግ የተከለከሉ ነገሮችን አለመያዝዎን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ከተጠቀሰው መጠን በላይ በጥሬው የያዙት የኢትዮጵያ ገንዘብ ካለ ራስዎን ፈትሸው ለሚሸኝዎ ሰው ወይም ለሌላ ሰው በአደራ ወይም በስጦታ ይስጡት። በፍተሻ ላይ ከተያዘ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘቡን ይዞ ከሀገር በመውጣት ወይም ወደ ሀገር በመግባት ወንጀል ያስጠረጥርዎታል። ምክንያቱም ብሔራዊ ባንካችን በተሰጠው ስልጣን መሰረት ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ ቁ FXD/01/2024 ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እና ከኢትዮጵያ የሚወጡ ተጓዦች ሊይዙት የሚችሉት የኢትዮጵያም ሆነ የውጭ ሀገር የገንዘብ ኖት መጠን ላይ ገደብ አስቀምጧል። ይህ የገንዘብ መጠን ገደብ በ2000 ዓ.ም በሥራ ላይ በነበረው መመሪያ ክልከላው በድፍኑም ሆነ በዝርዝር ከብር 200 (ሁለት መቶ ብር) በላይ የሚል ነበር። በተለያዩ ምክንያቶች አሁን ላይ ከላይ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ላይ ደርሷል። ይህ ገደብ ዋነኛ ዓላማው በሀገራችን ውስጥ የመገበያያ ገንዘባችን የሆነው ብር በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመነዘር የውጭ ሀገር ገንዘብ

የውጭ ሀገር ገንዘብ ሁሉ ገንዘብ ቢሆንም ለጠቀስነው መመሪያ ዓላማ ግን ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ መመንዘር የሚችሉ የውጭ ሀገር ገንዘቦች ብሎ ዕውቅና የሰጣቸው ገንዘቦች ናቸው የውጭ ምንዛሪ ወይም የውጭ ሀገር ገንዘብ የሚባሉት። የአሜሪካ ዶላር(በቀድሞው መመሪያም ላይ ቀዳሚ ነበር)፣ ተከታዮ በቀድሞው መመሪያ ላይ ዩሮ ነበር፣ በአዲሱ መመሪያ ላይ ከአሜሪካ ዶላር ቀጥሎ የተቀመጠው ፓውንድ ስተርሊንግ ሆኖ የቀድሞው ዮሮ ተከታይ ሆኖ በኢትዮጽያ ውስጥ የሚመነዘሩ የውጭ ሀገር ገንዘብነታቸው እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ሌሎች ብሔራዊ ባንክ ሚቀበላቸው ገንዘቦች ተብለው እና በስም ለጊዜው ያልተጠቀሱ ገንዘቦች በ4ኛ ደረጃ በብር ተመንዛሪ የውጭ ሀገር ገንዘብ ተብለው በመመሪያው ላይ ተጠቅሰዋል።

ፍቃድ ያለው ባንክ በተቀማጭነት እንዲቀበላቸው የተፈቀዱ ሌሎች በብር የሚመነዘሩ ገንዘቦች ደግሞ በቀድሞው መመሪያ ላይ "የእንግሊዝ ፓውንድ፣ የሳዑዲ ሪያል፣ የኩዌት እና የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ዲናር የነበሩ ሲሆን  በአዲሱ መመሪያ ላይ ደግሞ "የቻይና ዩዋን፣ የካናዳ ዶላር፣ የሳዑዲ ሪያል ፣የጃፓን የን፣ የአውስትሪያ ዶላር እና የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ድርሃም" ሌሎች በብር ተመንዛሪ የውጭ ሀገር ገንዘቦች ናቸው። እነኚህ ገንዘቦች ገቢ በተደረጉበት ስፍራ እና ጊዜ ባለው የምንዛሪ ተመን መሰረት የሂሳብ ቋቱ በተከፈተበት ገንዘብ ተመንዝረው ተቀማጭ ይደረጋሉ።

የውጭ ሀገር ገንዘብ ወደ ኢትዮጽያ ይዞ ስለመግባት እና ስለማሳወቅ

የውጭ ሀገር ገንዘብን በተመለከተ በኢትዮጵያ ነዋሪ ከሆኑ ወደ ግዛት ክልሏ ሲገቡ በጉዞ ሰነድዎ ላይ በስደተኞች እና በዜግነት አገልግሎት ማህተም ተረጋግጦ የገቡበት ቀን ተብሎ ከሚጠቀሰው ቀን አንስቶ በ30 ቀናት ውስጥ የያዙትን የውጭ ሀገር ገንዘብ በሙሉ ፍቃድ ባላቸው የምንዛሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የመመንዘር ወይም በባንክ በስምዎ በተከፈተ የውጭ ምንዛሪ ሂሳብዎ ገቢ የማድረግ ግዴታ አለብዎ።

የያዙት የውጭ ሀገር ገንዘብ ከ10,000 (አስር ሺህ) የአሜሪካን ዶላር ወይም ከዚያ ተመጣጣኝ ተመንዛሪ የውጭ ሀገር ገንዘብ በላይ ከሆነ ከዚህ መጠን በላይ የያዙትን የውጭ ሀገር ገንዘብ በውጭ ሀገር ምንዛሪ የባንክ ሂሳብዎ ገቢ ማድረግ ያለብዎት ሲሆን፤ ገቢ ሲያደርጉም የጉምሩክ ዲክላራሲዮን ወይም ወደ ሀገር የገባ የውጭ ሀገር ገንዘብ ማሳወቂያ መግለጫ ሰነድ ማቅረብ አለብዎት።

በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ነዋሪ ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወይም በሀገሪቱ ሕግ መሰረት በስደት እና በዜግነት ጉዳዮች አገልግሎት በኩል በኢትዮጵያ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት የመኖሪያ ፍቃድ የተሰጠው የውጭ ሀገር ዜጋ ማለት ነው።

የዘጠና ቀናት ገደብ

ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ሀገር ዜጋ ወይም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ መሆንዎን የሚያረጋግጥ የታደሰ መታወቂያ ካለዎት ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ማይኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሆኑ እና ከዘጠና ቀናት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የመቆየት ሀሳብ ካለዎት፤ የያዙትን የውጭ ሀገር ገንዘብ በሙሉ በጉዞ ሰነድዎ ላይ ከሚጠቀሰው ወደ ሀገር የገቡበት ቀን ጀምሮ በዘጠና ቀናት ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ያልሆነ ባለሂሳብ የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳብዎ ውስጥ ገቢ ማድረግ አለብዎት። የያዙት የውጭ ሀገር ገንዘብ ከ10,000 (አስር ሺህ) ዶላር በላይ ወይም የዚያ ተመጣጣኝ የውጭ ሀገር ገንዘብ ከሆነ ገንዘቡን በውጭ ምንዛሪ ሂሳብዎ ገቢ ሲያደርጉ ወይም በሕጋዊ መልኩ ሲመነዝሩ የጉምሩክ የውጭ ምንዛሪ ማሳወቂያ ሰነድ ማቅረብ አለብዎት።

የጉዞ ሰነድዎ ላይ ከተጠቀሰው የመግቢያ ቀን ጀምሮ በተቀመጠው ዘጠና ቀን ውስጥ ወደ ውጭ ሀገር የሚመለሱ ከሆነ ደግሞ የጉምሩክ የውጭ ሀገር ገንዘብ ማሳወቂያ ሰነዱ ላይ የተጠቀሰውን የውጭ ሀገር የገንዘብ መጠን ይዘው ከሀገር መውጣት ይችላሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የማይኖሩ የውጭ ሀገር ዜጋ ከሆኑ ደግሞ ይዘው የገቡትን የውጭ ሀገር ገንዘብ የተፈቀደልዎ የቪዛ ፍቃድ እስከ ፀና ድረስ በእጅዎ ማቆየት ይችላሉ።

ከባንክ የተገዛ የውጭ ሀገር ገንዘብ

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው ከባንክ የገዛው የውጭ ሀገር ገንዘብ ካለ የገዛበት ባንክ የሰጠው ደረሰኝ ላይ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ለ30 ቀናት ይዞ ማቆየት የሚችል ሲሆን፣ ከዚህ ቀን በኋላ ያሉት ሠላሳ ቀናት ከማብቃታቸው በፊት ግን ከባንክ የገዛውን የውጭ ሀገር ገንዘብ በሕግ በተፈቀደላቸው የምንዛሪ አገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ አቅርቦ ወደ ብር መመንዘር አለበት።

የሚመነዘር የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዞ ከሀገር ስለመውጣት

ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ሰው የውጭ ምንዛሪውን የገዛበትን እና ደረሰኙ ላይ ከተፃፈው ቀን ጀምሮ 30 ቀን ያላለፈው የውጭ ምንዛሪ ግዢ ደረሰኝ ካቀረበ በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ አንቀፅ 22(8)(2)(ሀ) መሰረት የውጭ ምንዛሪውን ይዞ ከሀገር መውጣት ይፈቀድለታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ያልሆነ ትውልደ ኢትዮጽያዊ ዲያስፖራ ወይም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የውጭ ምንዛሪውን የገዛበትን እና ደረሰኙ ላይ ከተፃፈው ቀን ጀምሮ 30 ቀን ያላለፈው የውጭ ምንዛሪ ግዢ ደረሰኝ ካቀረበ ወይም የጉዞ ሰነዱ ላይ ከተመዘገበው ቀን ጀምሮ ሲቆጠር ዘጠና ቀን ሳይሞላው ተመልሶ ከሀገር የሚወጣ ከሆነና ከ10 ሺ ዶላር በላይ ላለው የውጭ ሀገር ገንዘብ የጉምሩክ ማሳወቂያ ቅፅ ካቀረበ ይዞ የገባውን የሚመነዘር የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዞ መውጣት ይችላል።

ወደ ኢትዮጽያ የገቡ የኤምባሲ ሠራተኞች፣ ለተለያዩ የውጭ ሀገር ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞች፣ የአውደ ጥናት ተሳታፊዎች ወይም ሰልጣኞች ደግሞ ከ10,000 ዶላር በላይ መጠን ያለው የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዘው ከሀገር መውጣት የሚችሉት የባንክ የውጭ ምንዛሪ ደረሰኝ ወይም ከአሠሪያቸው ወይም ከአውደ ጥናቱ አዘጋጅ ገንዘቡ ከሕጋዊ ምንጭ ስለመገኘቱ የድጋፍ ደብዳቤ ሲያቀርቡ ብቻ ነው።

ወደ ሀገር ውስጥ የገባ የውጭ ምንዛሪን ማሳወቅ

ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ሰው፣ ትውልደ ኢትዮጽያዊ ዲያስፖራ፣ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ ያልሆነ የውጭ ሀገር ዜጋ ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት ላይ እያለ ከ10,000(አስር ሺህ) የአሜሪካ ዶላር ወይም ከተመጣጣኙ ተመንዛሪ የውጭ ሀገር ገንዘብ በላይ ከያዘ በአየር ማረፊያዎች ወይም ወይም በሌላ በማንኛውም ወደ ኢትዮጽያ መግቢያ ኬላ ላይ ሲደርስ ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀውን ቅፅ በመጠቀም የያዘውን የውጭ ሀገር ገንዘብ ማሳወቅ አለበት።

ከአስር ሺ ዶላር በታች የውጭ ሀገር ገንዘብ የያዘ ተጓዥ ግን የጉምሩክ ማሳወቂያ መሙላት አይጠበቅበትም።

ተላላፊ መንገደኞችን በተመለከተ ደግሞ ከማንኛውም የውጭ ሀገር ገንዘብን የተመለከተ ግዴታ ነፃ በመሆናቸው ማሳወቅም አይጠበቅባቸውም።

በኢትዮጵያ ውስጥ የማይመነዘር የውጭ ሀገር ገንዘብ

ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር ከሚጋሩ የጎረቤት ሀገራት በየብስ መጓጓዣ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ማንኛውም ሰው በድንበር ላይ ላለ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ወይም ጣቢያ ከ500 የአሜሪካ ዶላር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ወይም ከዛ በላይ በኢትዮጵያ የማይመነዘር የውጭ ሀገር ገንዘብ ከያዘ የያዘውን የገንዘብ መጠን የጉምሩክ የውጭ ምንዛሪ ማሳወቂያ መግለጫ ላይ በመሙላት ማሳወቅ ያለበት ሲሆን፤ ይህንኑ ያሳወቀውን የውጭ ሀገር ገንዘብ መጠንም ጉዳዩን ጨርሶ ሲመለስ ይዞ መውጣት ይችላል።

የውጭ ምንዛሪ ግብይት ክልከላ

በብሔራዊ ባንክ ወይም አግባብ ባለው ሕግ ካልተፈቀደለት በስተቀር ማንኛውም ሰው የውጭ ሀገር ገንዘብን በጥሬው ማስተላለፍ ወይም መክፈል አይችልም። በስጦታም ሆነ በእርዳታ ወይም ለግብይት ክፍያ ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ ወይም መክፈል አይችልም።

በብሔራዊ ባንክ ፍቃድ፣ በመመሪያው ወይም በሌላ ሕግ በተፈቀደው መሰረት ካልሆነ በቀር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የውጭ ምንዛሪ መያዝ አይፈቀድም። በብሔራዊ ባንክ ሚደረግበት አግባብ ተለይቶ ካልተፈቀደ በስተቀር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በውጭ ሀገር ገንዘቦች በማንኛውም መልኩ በጥሬው መገበያየት አይፈቀድም።

አምስት ሺ ዶላር በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ

እንደ ማሳያ ይሆነን ዘንድ እስከ ፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ ውሳኔ ያገኘንና ካዲሱ መመሪያ ጋር ብዙም ለውጥ በሌለው የቀድሞው የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሰረት የውጭ ምንዛሪን በሕገ ወጥ መንገድ ይዞ የተገኘን የአንድ ግለሰብን የሚመለከት ጉዳይ እናንሳ።

አንድ ግለሰብ መገናኛ አካባቢ ባለው የከተማ ባቡር ፌርማታ ህዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም ሊሳፈር ሲል ፖሊሶች ባደረጉት ፍተሻ 5000 የአሜሪካ ዶላር ይዞ ተገኘ። የውጭ ምንዛሪ ማሳወቂያ ሰነድ ሲጠየቅም ሊያቀርብ ስላልቻለ በሕገ ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪ ይዞ በመገኘት ወንጀል ተከሰሰ። ግለሰቡ ለክሱ በሰጠው ምላሽ ዶላሩን መያዝ ይዣለሁ፤ የያዝኩት ግን አንዲት ኩዌት ነዋሪ የሆነች ወጣት ወላጅ እናቷን ማሳከሚያ እንዲሆን በወ/ሮ አልማዝ በኩል ልካው ከግለሰቧ እጅ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ቦሌ ኤርፖርት በአደራ የተቀበልኩት በመሆኑ በወንጀል ልጠየቅበት አይገባም አለ። ምስክሮችም አቅርቦ ይህንኑ አስረዳ።

ክሱ የቀረበለት የፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤትም በወቅቱ በስራ ላይ የነበረውን የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ጠቅሶ ግለሰቡ ከሌላ ሰው በአደራ ተቀበልኩት ቢልም ገንዘቡ ወደ ሀገር ሲገባ የውጭ ምንዛሪ ማሳወቂያ መግለጫ አልተሰጠበትም። በዚያ ላይ ጥቅምት 30 ተቀበልኩ እያለ፣ እስከተያዘበት ህዳር 17 ዶላሩን ይዞ በማቆየቱ አጥፍቷል። ሕጉን አለማወቁም ከተጠያቂነት አያድነውም ብሎ ጥፋተኛ ነህ አለውና በሦስት ዓመት ፅኑ እስራትና በአስር ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ፈረደበት።

ግለሰቡ ይግባኝ ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት ስላላገኘ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ሲል የሰበር አቤቱታ ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀርባል። ሰበር ሰሚ ችሎቱም ህዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ያልታተመ የሰበር ውሳኔ ላይ እንዳሰፈረው የግለሰቡን ቅሬታ መርምሮ የስር ፍ/ቤት በሰጠው ውሳኔ እስማማበታለሁ፤ ምንም የሕግ ስህተት አልተፈፀመም ብሎ የስር ፍ/ቤቱን ውሳኔ አፅንቶታል።

ለማንኛውም ከሀገር ሲወጡም ሆነ ወደ ሀገር ሲገቡ በሕግ ከሚፈቀድልዎ በላይ ብርም ሆነ የውጭ ሀገር የገንዘብ ኖት አለመያዝዎን ያረጋግጡ። የውጭ ሀገር ገንዘብን በተመለከተ ባግባቡ ማሳወቂያ መግለጫ መሙላትዎንና በሕጉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በሕጋዊ መንገድ ወደ ብር መመንዘርዎን ወይም በውጭ ምንዛሪ የባንክ ሂሳቦ ገቢ ማድረግዎን አይዘንጉ። የውጭ ምንዛሪ ሲገዙም ሆነ ሲሸጡ ሕጋዊውን የግብይት አማራጭ ብቻ ይጠቀሙ። ተገቢነት ያለውን ማስረጃ መያዝዎንም ያረጋግጡ።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top