የክረምት ወቅትን ተከትሎ ከሚከሰቱ አደጋዎች ህብረተሰቡ ራሱን ሊጠብቅ ይገባል፦ የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን

8 Mons Ago 912
የክረምት ወቅትን ተከትሎ ከሚከሰቱ አደጋዎች ህብረተሰቡ ራሱን ሊጠብቅ ይገባል፦ የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን
ህብረተሰቡ የክረምት ወቅትን ተከትሎ ከሚከሰቱ አደጋዎች የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል።
 
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ባለፉት የክረምት ጊዜያት ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋዎች አጋጥመው በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
 
ከሰሞኑ የሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ ባወጣው መረጃ መሰረት ከባድ ዝናብ፣ የመሬት መሸራተት እንዲሁም የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፤ አደጋው ሊከሰትባቸው ይችላል የተባሉ አካባቢዎችም ተጠቅሰዋል።
 
በክረምቱ አደጋ ሊከሰትባቸው ይችላሉ ተብለው ከተጠቀሱ ቦታዎች ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አንዷ መሆኗን የገለጹት አቶ ንጋቱ፤ ይህንን የአደጋ ስጋት ለመቀነስ ኮሚሽኑ በከተማ ደረጃ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
 
በከተማዋ በከፍተኛ ደረጃ ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ያሉ ነዋሪዎችን ከስፍራው እንዲነሱ እንዲሁም በወንዝ ዳርቻ አካባቢዎች የጎርፍ መከለያ ግንቦች እንዲሰሩ በማድረግ የቅድመ መከላከል ስራዎችን በመስራት ኮሚሽኑ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
 
በወንዝ ዳርቻ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን በተደጋጋሚ ከስፍራው የማስነሳት ስራ ቢከናወንም፤ አንዳንዶች ወደ አካባቢው ስለሚመለሱ ስራውን አስቸጋሪ እያደረገው ነው ብለዋል የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው።
 
በፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ምክንያት የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመከላከል ኮሚሽኑ ለሚመለከታቸው ተቋማት በማመላከት፣ስራው በሚከናወንባቸው አካባቢዎች መነሳት ያለባቸው ቤቶች ተነስተው የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ዝርጋታዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።
 
ህብረተሰቡ ራሱን ከጎርፍ አደጋ እንዲጠብቅ በተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ ንጋቱ ተናግረዋል።
 
ከግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው በተጓዳኝ አደጋው ቢያጋጥም በአስሩም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና ማዕከላት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች እና የአደጋ ጊዜ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች በተጠንቀቅ ላይ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል።
 
የክረምት ወቅት መሆኑን ተከትሎ ህጻናት እና ታዳጊዎች እረጅም የእረፍት ጊዜ ላይ በመሆናቸው፣ ለመዋኘት እና ለመታጠብ በሚል ወደ ወንዞች እና ኩሬዎች ገብተው ሕይወታቸውን እንዳያጡ ከህብረተሰቡ ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራን ነው ብለዋል አቶ ንጋቱ።
 
በዚህ ዙሪያ በከተማ ደረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ የጥንቃቄ መልክቶችን ከግንዛቤ በማስገባት ራሱን እና ቤተሰቡን ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top