በአዲሱ በጀት ዓመት ከዚህ ቀደም ያልተሳኩ ዕቅዶችን ለማካካስ ዝግጅት ተደርጓል፡ - የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

1 Mon Ago 222
በአዲሱ በጀት ዓመት ከዚህ ቀደም ያልተሳኩ ዕቅዶችን ለማካካስ ዝግጅት ተደርጓል፡ - የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
በአማራ ክልል በአዲሱ 2017 በጀት ዓመት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ችግሮች ያልተሳኩ ዕቅዶችን ለማካካስና የበጀት ዓመቱን ዕቅድ በአግባቡ ለመፈጸም ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገልጸዋል።
 
የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 ዕቅድ የውውይት መድረክ መካሄድ ጀምሯል።
 
በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
 
ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፤ በክልሉ ያጋጠሙ ችግሮችን ወደ ዕድል በመቀየር ክልሉን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር የቁጭት ዘመን ዕቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
 
የ2016 በጀት ዓመት ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ያለፈው የፀጥታ ችግሮችን በመቅረፍ መረጋጋትን የማስፈን ስራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
 
በዚህም ለልማት ምቹ ምህዳር የመፍጠር ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፥ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች በግብርናና ሌሎች መስኮች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
 
ዘላቂ ሰላምን የመገንባት፣ የመልካም አስተዳደር ሥራን የማስፈን ተግባራትም መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
 
በአዲሱ 2017 በጀት ዓመትም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ችግሮች ያልተሳኩ ዕቅዶችን ለማካካስ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
 
የ2017 በጀት ዓመት ትኩረት ሰላምን በየአካባቢው በማረጋገጥ ለቀጣይ ዓመታት የልማት ሥራዎች አስተማማኝ መሠረት መጣል እንደሆነም ጠቅሰዋል።
 
ለዚህም በርካታ ጠመዝማዛ መንገድን ማለፍ እንደሚጠይቅ አመራሩ መገንዘብ አለበት ብለዋል።
 
በተለይም አመራሩ ችግሮችን በልዩ ትኩረት፣ በቅንጅትና በትብብር መሻገር እንዳለበት አሳስበዋል።
 
ሥራችን የህዝብን ጥያቄ የመመለስና የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ህዝቡን ለሰላምና ለልማት ማስተባበር እንደሚገባ አንስተዋል።
 
ክልሉ ያለውን የወደፊት የልማት ርዕይ በዝርዝር ያካተተ ስትራቴጂክ ፎኖተ ካርታና ዕቅድ ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
 
ዕቅዱ በማክሮ ደረጃ ያሉ ጥንካሬና ድክመቶችን በመለየት የተዘጋጀና ከ2018-2022 ዓ.ም የሚተገበር የቁጭት ዘመን ዕቅድ ነው ብለዋል።
 
የአማራ ክልልን ከግጭት ማግስት ወደ ስኬት ለማሻገር ዕቅዱ ወሳኝ በመሆኑ፥ በ2017 በጀት ዓመት ምቹ መሠረት መጣል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
 
ለዚህም አመራሩ የጋራ መግባባት በመፍጠር ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መነሳትና ህብረተሰቡን ማስገንዘብ የዚህ በጀት ዓመት ትልቅ ስራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ያጋጠመንን ችግር ወደ ዕድል በመለወጥ ክልሉን ለማሻገር ህዝብን ያሳተፈ ሰፊ ርብርብ ወሳኝ ነው ብለዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top