• የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመምህራን ብቁ መሆን ወሳኝ ነው፡- የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ • የመምህራን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከትምህርት ጥራት መጠበቅ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡- የመምህራን ማህበር

5 Mons Ago 604
• የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመምህራን ብቁ መሆን ወሳኝ ነው፡- የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ • የመምህራን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከትምህርት ጥራት መጠበቅ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡- የመምህራን ማህበር
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የመምህራን ብቁ መሆን ወሳኝ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዓሊ ከማል ገለፁ፡፡
 
በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች መምህራንን የማብቃት ስራ እንደሚሰራ ያነሱት ኃላፊው፤መምህራን ዋነኛ ኃላፊነታቸው ራሳቸውን ከጊዜው ጋር የዋጀ ማድረግ ነው ሲሉ ይገልፃሉ፡፡
 
ኃላፊው ለመምህራን የማስተማር ሥነ-ዘዴን ጨምሮ ብቁ ሊያደርጓቸው የሚችሉ ስልጠናዎች እንደሚሰጣቸው ጠቁመው፤ ከዚህ በተጨማሪ በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ባሉ ርዕሰ መምህራን እንዲገመገሙ እና ያለባቸውን ክፍተት በስልጠና እንዲሞሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
 
መማር ያቆመ መምህር ማስተማር እንዳቆመ ይወሰዳል ያሉት ኃላፊው፤ ተቋሙ በዋናነት ብቁ የሆኑ እና ከመጪው ትውልድ ጋር ራሳቸውን ማስኬድ የሚችሉ መምህራንን ማብቃት ዓላማው መሆኑን ገልጻሉ፡፡
 
ይህ እንቅስቃሴ ለሙያው በቂ ፍላጎት በሌላቸው አካላት እንደሚፈተን በመግለፅ፤መምህርነት ትልቅ ጥረትን እና የማወቅ ፍላጎትን የሚፈልግ ሙያ ነው ይላሉ፡፡
 
የመምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሃንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረጉ ለውጦች መምህራንን ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡
 
ኢኮኖሚያዊ ጫና ከመምህራን የማስተማር ሂደት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለውም ይገልጻሉ፡፡
 
የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ በጫና ውስጥ ያሉ መምህራን የተጣለባቸውን ተማሪዎችን የማብቃት ኃላፊነት ትኩረት በመስጠትና በጥራት ይወጣሉ ማለት አዳጋች እንደሆነ ነው የሚያስረዱት፡፡
 
የአንድን ሃገር የትምህርት ጥራት ደረጃ ለማሻሻል ለመምህራን ከሚሰጠው ስልጠና ባሻገር ኢኮኖሚዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ፡፡
 
አክለውም መምህራን ከደሞዝ ማሻሻል ባሻገር የተለያዩ ማበረታቻዎች ሊደረግላቸው እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
 
የትምህርት ጥራትን አስመልክቶ በሃያ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የበይነ መረብ ስልጠና መሰጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡
 
በዚህ ስልጠና መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በበይነ መረብ ባደረጉት ንግግር "የትውልድ ቅብብል የተሳካ የሚሆነው መምህራን በሚወጡት እጅግ ጠቃሚ ሚና ነው" ማለታቸው የሚታወስ ነው።
 
በ36ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይም "የሀገር ምሰሶ ለሆኑት ወታደር እና መምህራን የሚገባቸውን ባይሆንም የምንችለውን በማድረግ ሕይወታቸውን ለማሻሻል እንሰራለን" ሲሉ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top