እውነት እና እውነትን ብቻ መመስከር

1 Mon Ago 624
እውነት እና እውነትን ብቻ መመስከር

ፍትሕ እንዳትዛባና ሕግ እንዲከበር የሚፈልግ ዜጋ በወንጀልም ሆነ በፍትሐ-ብሔር የክስ ሂደት ላይ የሚያውቀውን ነገር በእውነት መመስከር አለበት።

በነዚህ ሂደቶች ውስጥ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ የሕግ ባለሞያዎች ሥራዬ ብለው የሚወጧቸው ሚናዎች አሉ፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ እንደ አንድ የሕብረተስቡ አባል እውነት እንዲወጣ ስለጉዳዩ ምናውቀውን ለሕግ አካል  የመግለፅ የህሊና ብሎም እንደየሁኔታው የሕግ ግዴታ አለብን፡፡

በማንኛውም የሙግት ሂደት ላይ እውነቱ የሚነጥረው ስለ አከራካሪው ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በሌላ መልኩ የሚያውቁ ሰዎች በሚሰጡት ማስረጃ ነው፡፡

ከነዚህ የማስረጃ ዓይነቶች ውስጥ አንዱ የሕብረተሰቡ አባላት ስለጉዳዩ ያዩትን፣ የሰሙትን ወይም በተለያየ መንገድ ያወቁትን ነገር በተመለከተ የሚሰጡት የነባሪነት፣ የእማኝነት ወይም የምስክርነት ቃል ነው፡፡

ማንኛችንም ነባሪ በነበርንበት የፍትሐ-ብሔር ጉዳይ ላይ ለፍትሕ ስንል ነገሩን በእማኝነት ማረጋገጥ ብሎም ወንጀል ከተፈፀመ ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ሕጋዊ ግዴታችንን መወጣቱና የሕግ አካል ሲጠይቀን የምናውቀውን በትክክል መግለፅ ማህበረሰቡ ውስጥ ወንጀል እንዳይስፋፋ፤ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና ጥፋተኞች ለሕግ እንዲቀርቡ የምናደርገው ማህበራዊና ሕሊናዊ ግዴታችንም ጭምር ነው፡፡

በተለይ አንዳንድ ወንጀሎችን ዓይቶ እንዳላየ ማለፍ በራሱ ብቻውን በሕግ ያስጠይቃል፡፡ ሆኖም ግን ማንኛውም ሰው በማስረጃነት ቀርቦበት ሊያስወነጅለው በሚችል ጉዳይ ላይ ግን በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 19 (5) መሰረት የወንጀል ጥቆማ እንዲያቀርብ ወይም ምስክርነት እንዲሰጥ አይገደድም፡፡

በወንጀልም ሆነ በፍትሐ-ብሔር ጉዳዮች ላይ ለምስክርነት ስንጠራም እነኚህን ጉዳዮች ልብ ማለት እና ሕግ የጣለብንን ግዴታ መወጣት ይጠበቅብናል።

 1. መጥሪያን መቀበል

የሚላክልን መጥሪያ ለምን ጉዳይ፣ መቼ እና የት እንደተጠራን ይገልፅልናል። ስለ ጉዳዩ እንኳን ባናውቅ የተላከልንን መጥሪያ አልቀበልም ማለት አይገባም፡፡

ፍርድ ቤቱ መጥሪያ   አልቀበልም ማለታችንን ካረጋገጠ ታስረን በግድ እንድንቀርብ ትዕዛዝ ሊያስትላልፍብን ይችላል። ስለዚህ ግልፅ ያልሆነልን ወይም መጥሪያው አይመለከተኝም የምንል ከሆነ መጥሪያውን ተቀብለን በቀጠሮው ቀንና ሰዓት ቀርበን ማስረዳት ወይም ማጣራቱ ተገቢ ነው።

 2. ቀጠሮ ማክበር

ማንኛውም መጥሪያ ከደረሰን በቀጠሮው ቀንና ሰዓት በፍርድ ቤቱ መገኘት አለብን። በፍርድ ቤቱ ስንጠራም በአካል መቅረብ እና መቅረባችንን ማሳወቅ አለብን። ፍርድ ቤቱ ሳያሰናብተንም ችሎቱን ለቅቀን መሄድ አንችልም፡፡

 3. ጣቢያም ልንጠራ እንችላለን

በወንጀል ጉዳይ መርማሪው ፖሊስም ሊጠራን ይችላል። ቀርበን እውነተኛውን መልስ የመስጠት ግዴታ አለብን፡፡ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 30 መሰረትም በወንጀል ራሳችንን የሚያስጠይቀን ጉዳይ ላይ ብቻ ነው መልስ አልሰጥም ማለት የምንችለው፡፡

 4. ማስረጃ እንድናቀርብ ልንታዘዝ እንችላለን

በፍትሐ-ብሔር ጉዳይ ላይ በእጃችን የሚገኘውን ማስረጃ እንድናቀርብ፤ የምስክርነት ቃላችንን እንድትሰጥ ወይም በጉዳዩ ላይ ባለን ልዩ ዕውቀት የባለሙያ ምስክርነት እንድንሰጥ ልንጠራ እንችላለን።

የፅሁፍ ማስረጃ እንድናቀርብ ከሆነ የታዘዝነው ማስረጃውን ከመዝገቡ ጋር ካያያዝን እኛ በአካል ባንቀርብም ግዴታችንን እንደተወጣን ይቆጠርልናል።

 5. ምስክርነት አበል አለው

በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 212 መሰረት ለምስክሮች ለመጓጓዣና ለሌላም የቀን ወጪ አበል ለባለሙያ ምስክር ደግሞ ለሙያው የሚገባውን ተጨማሪ አበል ምስክሩን የጠራው ወገን በፍርድ ቤቱ በኩል እንደሚከፍል ይደነግጋል፡፡ ሕጉ ይህን ያደረገው እንደ ምስክር እውነቱን እንድንናገር እና በሌላ ሰው ጉዳይ ወጪ እንዳናወጣ ነው፡፡

 6. ጉዳዩ እስኪያልቅ መታገስ

ፍርድ ቤቱ በቃኝ ብሎ ካላሰናበተን ጉዳዩ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ በቀጠሯችን ቀን መቅረባችንን መዘንጋት የለብንም። በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 120 ላይ የተጣለብን ግዴታ ነው፡፡ በቀጣዩ ቀጠሮ ለመቅረባችን ዋስ ካልጣራን ወይም ፍ/ቤቱ የመቅረባችንን ነገር አጠራጣሪ ከመሰለው 120 እና 121 መሰረት ማረፊያ ቤት እንድንቆይ ሊያዝብን ይችላል፡፡

ምስክርነት ሕጋዊ ግዴታ በመሆኑ ለምስክርነት ፍርድ ቤት ለምንቆይበት ሰዓት አሠሪ ለሠራተኛው ደሞዝ የሚከፈልበት የምስክርነት ፍቃድ መስጠት ያለበት ሲሆን፤ ምስክሩም ምስክርነት ከተጠራበት የዳኝነት አካል የምስክርነት መጠራቱን እና የቆየበትን ጊዜ የሚያሳይ ማስረጃ ለአሠሪው ማቅረብ አለበት።

  7. ከተጠራን መቅረብ ግድ ነው

በወንጀል ጉዳይ ላይም የዐቃቤ ሕግ ወይም የተከሳሽ ምስክር ሆነን በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 124 አና 125 በምስክርነት ከተጠራን ቀርበን መመስከር ግዴታችን ነው። አልያ በፖሊስ ታስረን እንድንቀርብ ሊታዘዝብን ይችላል፡፡

  1. ምሎ የመመስከር ኃላፊነት

በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 136 እና በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 261(1) መሰረት የምንሰጠው ምስክርነት እውነት መሆኑን በመሓላ ቃል እናረጋግጣለን፡፡ በመሓላ የሰጠነው ቃል ሀሰት ሆኖ ቢገኝ ግን ተጠያቂነቱ በምናምንበት እምነት ብቻ ሳይሆን እውነቱን ለመናገር ምሎ በሀሰት መመስከር በወንጀልም ጭምር ያስጠይቀናል። በተለይም በወንጀል ጉዳይ ላይ ቅጣቱ የሀሰት ምስክርነቱ ንፁህ ሰው ላይ ባስከተለው ቅጣት መጠን ድረስ ሊደርስ ይቸላል፡፡

 9. ስለ ራስ መመስከር

በፍ/ብሔር ጉዳይ ላይ ከሳሽ ወይም ተከሳሸ በራሳቸው ጉዳይ ላይ ምስክርነት መስጠት እንደሚችሉ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉ 261(2) ይፈቅዳል፡፡ በወንጀል ጉዳይ ላይ ደግሞ የግል ተበዳይ ስለተፈፀመበት ወንጀል መመስከር ይችላል።

 10.መሓላ

የምስክርነት መሓላ በፍርድ ቤቶቻችን ከሃይማኖቶች ጋር ተያይዟል፡፡ በመሆኑም ቃለ መሓላ ሚፈፀምባቸው መጽሐፍ ቅዱስ እና ቁርአኖች በየችሎቶቹ ይገኛሉ።

ምስክሮች ለምስክርነት የሚምሉትም ሃይማኖታቸውን ተጠይቀው ክርስቲያኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ሙስሊሙ በቁርአን ላይ እጅ ጭነው ነው፡፡

ይህ ግን ከልማድ የመነጨ አሠራር ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሁሉንም እምነቶች ይወክላል ሊባል የሚችል አይደለም። በመሆነም ቅዱሳን መጽሐፍቱ ከሚወክሏቸው እምነቶች ውጭ ያሉ እምነቶችን የሚከተሉ ወይም እምነት የሌላችው ምስክሮችን የምስክርነት ቃል በመሓላ ማረጋርገጥን አስቸጋሪ ያደርገዋል። የ/ፍ/ብ/ሥ/ሥ/ ሕጋችንም ቢሆን ምስክር መማል ያለበት እንዲህ መሆኑን አስቀምጧል።

"በዚህ ፍርድ ቤት ፊት የምሰጠው ቃል እውነት፤ በሙሉ እውነትነት፤ እውነት እንጂ ሌላ ምንም እንደማይሆን እምላለሁ ወይም አረጋግጣለሁ፡፡"


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top