የኦሎምፒክ አይረሴ ትዝታዎች፤ ከበርሊን እስከ ቶኪዮ አስገራሚ ክስተቶች ምን ነበሩ?

2 Mons Ago 1002
የኦሎምፒክ አይረሴ ትዝታዎች፤ ከበርሊን እስከ ቶኪዮ አስገራሚ ክስተቶች ምን ነበሩ?

ከ100 ዓመታት በላይ፣  በየአራት ዓመቱ፣ ከ200 በላይ  ሀገራት የተውጣጡ እጅግ አስደናቂ አትሌቶች  በአንድ ሀገር  ከትመው  ከ300 በላይ ውድድሮች ባሉት በዘመናዊው  የኦሊምፒክ  ጨዋታዎች  ይሳተፋሉ።

ታዲያ በኦሎምፒክ መድረክ  ጨዋታዎቹ  ብዙ አዳዲስ ክስተቶች  ይስተዋላሉ። ከማይታመን የዓለም ሪከርዶች  እና አሸናፊዎች እስከ አስደንጋጭ እና ደፋር የፖለቲካ ተቃውሞዎች ድረስ ታሪክ ይመዘገብባቸዋል።

እኛም ዛሬ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ አርፈን በቅርብ ርቀት ካለፉት ከዓለም ትልቁ የስፖርት ውድድር ኦሎምፒክ  ስክሪኖቻችንን ያስደመሙትን የማይረሱ የመድረኩ ታሪኮችን መለስ ብለን እንቃኛለን።

*****************************************

  1. በ1936 የበርሊን ኦሎምፒክ ጄሴ ኦውንስ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸነፈ።

በጀርመን  በናዚ አገዛዝ ውጥረት ውስጥ በነበረበት ወቅት በተካሄደው ኦሊምፒክ አሜሪካዊው የትራክ አትሌት ጄሲ ኦውንስ በ100 ሜትር፣ በ200 ሜትር፣ በ4x100 ሜትር እና በረጅም ዝላይ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘቱ አድናቆትን አስተናግዷል።

ይህም በአውሮፓውያኑ 1936ቱ ጨዋታዎች እጅግ ስኬታማ አትሌት ሲያደርገው በአንድ ኦሎምፒክ አራት የትራክ እና የሜዳ ወርቅ በማሸነፍ የመጀመሪያው አሜሪካዊ እንዲሆንም አስችሎታል። ጀርመን በ1936 ኦሎምፒክ የነጭ የበላይነትን ለማሳየት አቅዳ የነበር ቢሆንም ኦውንስ ይህንን  እቅዷን በስራውና በብቃቱ አስቁሞታል።

  1. በ1948ቱ የለንደን ኦሎምፒክ ቪኪ ድራይቭስ በውሀ ዋና ዳይቪንግ የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ለማሸነፍ የመጀመሪያዋ እስያ-አሜሪካዊ ሆነች።

በአውሮፓውያኑ 1924 ከፊሊፒናዊ አባት እና እንግሊዛዊ እናት የተወለደችው ቪኪ ድራቭስ በብሄሯ ዙሪያ የሚደርስባትን መድልዎ እና ጭፍን ጥላቻ እየታገለች ነው ድሏን ያሳካችው። ድራቭስ በ1948ቱ  የኦሎምፒክ ጨዎታዎች ከምርጥ አትሌቶች አንዷ በመሆንም ተመርጣለች።

  1. በ1960 በሮም ኦሎምፒክ ዓለም አዲስ ጀግናን በሩጫው ሜዳ ተዋወቀች እሱም ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ነው።

በባዶ እግሩ በመሮጥ የማራቶን ሻምፒዮን የሆነው አበበ ቢቂላ በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያው አፍሪካዊም ነው። አበበ ቢቂላ ምን አጋጥሞት ይሆን በሰው ሀገር በባዶ እግሩ ትልቁን የስፖርት ድግስ የተካፈለው ሲሉ ብዙዎች ይጠይቃሉ ።

ኢትዮጵያዊው የማራቶን ሯጭ አበበ ቢቂላ ግን ከሀገሩ ወደሮም ሲሄድ ጫማ እዛው አገኛለሁ ብሎ አስቦ ቢሄድም በሮም ለሱ የሚመጥነው ጫማ ማግኘት አልቻለም። ታዲያ አበበ ቢቂላ ነገሩ ግራ ቢገባው ለራሱ ከኢትዮጵያ ይዟቸው ሮም የዘለቀውን ጫማዎች ለሩጫው ለማድረስ ሞከረ ግን አልሆነም አልተሳካለትም። አበበ በሀገሩ በባዶ እግሩ የመራመድንና የመሮጥ ልምድ ነበረውና  ጫማ ባያገኝም ለሀገሩ ክብር በባዶ እግሩ ለመሮጥ ወሰነ።

ታዲያ ከሁሉም በተለየ የሀገሩን ክብር አስቀድሞ ያለጫማ በባዶ እግሩ ለሩጫ የተሰለፈው ጥቁሩ አበበ ቢቂላ ነጮቹን አስከትሎ የርቀቱን ሪከርድ በመስበር ጭምር አሸነፈ።  ብዙዎችም በኦሎምፒክ ታሪክ የተመዘገበ የሀገር ፍቅርና አልሸነፍ ባይነት መንፈስ ማሳያ ሲሉ በታሪክ መዝገብ ስሙን አሰፈሩት። በዛው የ1960 የሮም ኦሎምፒክ ዊልማ ሩዶልፍ በትራክ እና በነጠላ ጨዋታዎች ሶስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘቷ የመጀመሪያዋ አሜሪካዊት ሆናለች።

  1. በ1968 ሜክሲኮ ሲቲ ኦሎምፒክ፦ ቶሚ ስሚዝ እና ጆን ካርሎስ የማይረሱ ናቸው ይለናል የታሪክ አምድ

በአውሮፓውያኑ 1968 በሜክሲኮ ሲቲ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች አፍሪካ አሜሪካውያን አትሌቶች ቶሚ ስሚዝ እና ጆን ካርሎስ በ200 ሜትር የሩጫ ውድድር ወርቅ እና ነሐስ አሸንፈው ሲወጡ ስሚዝ  አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።

ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ከሞተ በኋላና የ1968 የሲቪል መብቶች ህግ ከፀደቀ ከወራት በኋላ በአሜሪካ ውስጥ የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴ ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት በነበረበት ወቅት ነበር ውድድሩ የተካሄደው ታዲያ በመድረኩ ሁለቱ አትሌቶች ድላቸውን ተከትሎ አንገታቸውን ደፍተው፣ ጫማ የሌለው ጥቁር ካልሲ ለብሰው፣ የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር እያንዳንዳቸው ጥቁር ጓንት አድርገው መልዕክታቸውን አስተላለፉ። ስሚዝ ጥቁር ሃይልን ለመወከል የቀኝ እጁን አነሳ። ካርሎስ ጥቁር አንድነትን ለመወከል የግራ እጁን አነሳ።

ይህን አስደናቂ ተቃውሞ ተከትሎ የአለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስሚዝን እና ካርሎስን አወገዛቸው። ከአሜሪካ ቡድን ታግደው ከቀናት በኋላ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አደረጋቸው። በመገናኛ ብዙኃን ተሰደቡ ተንቋሸሹ ለወደፊቱ ውድድር እንዳይካፈሉ ጭምር ተከለከሉ። በዘመናዊው የኦሎምፒክ ታሪክ ውስጥ ታዲያ በጣም ኃይለኛ የፖለቲካ መግለጫዎች አንዱ ተብሎ የሚታሰብ ድርጊት በማድረጋቸው ስማቸው በታሪክ መዝገብ ሰፍሮ ይገኛል።

  1. ሌላኛው በስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ የማይረሳው የ2008 የቤጂንግ ኦሎምፒክና ክስተቶቹ ናቸው።

በዚህ ኦሎምፒክ ዓለም የሰው አቦሸማኔ የሚል ቅፅል ስም የወጣለትን  የዓለማችን ፈጣኑን አትሌት ዩዜን  ቦልትን ተዋውቃለች። በ2008 ዩሴን ቦልት ከየት እንደመጣ ሳይታወቅ የዓለማችን ፈጣን ሰው ሆነ የሚሉት ብዙ ናቸው።

ቦልት በ2004 የአቴንስ  ኦሎምፒክ በ200  እና 400 ሜትር ባደረገው ተስፋ አስቆራጭ የመጀመሪያ ውድድር ባይሳካለትም አሰልጣኞቹን አሳምኖ ወደ 100 ሜትር  ውድድር ከገባ በኋላ ብዙ ክብረወሰኖችን መስበር ችሏል በ2008 ኦሎምፒክ ጥቂት ወራት ሲቀረው ቦልት በመሮጥ የዓለም ሪከርድ ባለቤት የሆነውን አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ በ100 ሜትር ፉክክር  አሸንፏል። 

ታዲያ በዚህ አላበቃም 9.72 ሰከንድ በሆነ አዲስ የአለም ሪከርድ የነበረው ቦልት  በቤጂንግ የራሱን ሪከርድ ወደ 9.69 በማውረድ በማሸነፍ ታሪክ ፅፏል። ይህ የቦልት የ100 ሜትር የበላይነት  በ2009 የዓለም ክብረ ወሰን ወደ 9.58 ዝቅ አስደርጎታል። ሪከርዱም እስካሁን በማንም አትሌት አልተደፈረም። የቤጂንግ ኦሎምፒክን አይረሴ ካደረጉት መካከል ይህ የአጭር ርቀት ሯጭ አንዱ ነው።

  1. የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ

በከፍታ ዝላይ የወርቅ ሜዳሊያ ሁለት አትሌቶች የተጋሩበት ክስተት በመድረኩ የሚረሳ አልነበርም። ሙታዝ ኢሳ ባርሺም ከኳታር እና ጂያንማርኮ ታምበሪ ከጣሊያን ነበሩ የወርቅ ሜዳሊያውን በጋራ የወሰዱት።

ሁለቱም ከጨዋታው በፊት የጅማትና የቁርጭምጭሚት ህመም ሲፈትናቸው የነበረ ቢሆንም ያንን ተቋቁመው ነው  በከፍታ ዝላይ የ2.37 ሜትር በማስመዝገብ ታሪክ መስራት የቻሉት።

 

አስገራሚው ነገር ሁለቱም የኦሎምፒክን የ2.39 ሜትር ሪከርድ ለመስበር ሶስት ያልተሳኩ ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ፣ ሁለት አማራጮች ነበሯቸው። ሁለቱ አትሌቶች ታሪካዊ የሆነውን የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ለመካፈል በመወሰን ሜዳልያ ተጋርተዋል።

በዚህም ከ1912 ጀምሮ በአትሌቲክስ ውድድር የመጀመሪያው የጋራ የኦሎምፒክ ወርቅ አሸናፊ በሚል ስማቸው በታሪክ መዛግብት እንዲሰፍር ሆኗል።

ኦሎምፒክ ሁሉም ሀገር እራሱን የሚገልፅበት በውድድሩ ድመቀት የሰዎች ልብ የሚንጠለጠልበት ትልቅ መድረክ ነው። በኦሎምፒክ ታሪክ አስደናቂ ሁነቶች ብዙ ናቸው። ጥቂቶቹን  መርጠን አካፈልናችሁ። በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክስ ምን እንመለከት ይሆን?  የሚቀጥሉት 16 ቀናት መልስ ይዘው ይመጣሉ።

በናርዶስ አዳነ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top