ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፓሊሲ ትግበራ ገባች

1 Mon Ago 1824
ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፓሊሲ ትግበራ ገባች
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ፖሊሲ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
 
****************************
 
የ2010 ዓ.ም የፖለቲካ ለውጥን ተከትሎ መንግሥት አያሌ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራትን አከናውኗል። ባለፉት ጊዜያት የተከማቹ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት ላለፉት ስድስት ዓመታት ማሻሻያዎችን ሲያደርግ እንደቆየ ይታወቃል። የዕዳ ጫና፣ ገና ብዙ ሥራ የሚፈልገው የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ አዝጋሚ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ዝቅተኛ የዘርፎች ምርታማነት፣ ዝቅተኛ የልማት ፕሮጀከቶች አፈጻጸምና የሀብት ብክነት፤ የተረከባቸው ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕዳዎች ናቸው።
 
የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ ሂደቶቹ ኢኮኖሚው ወደ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ አንዲሸጋገር አዲስ ተስፋን አምጥተዋል። በ2011 በጀት ዓመት ወደ ትገበራ የገባው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ብዙ የፖሊሲ ሐሳቦችን በውስጡ ያካተተ እና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዓላማዎችንና ግቦችን ያሳካ ነበር። ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም፤ የማከሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማረም፣ የዕዳ ጫናን ለማቃለል፣ የሀገር ውስጥ የማምረት ዐቅምን ለማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለማረም በተደረገው ጥረት ውጤቶች ተገኝተዋል።
 
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያሳዩ ካሉ ሀገራት አንዷ ሆናለች። ከ2010 እስከ 2015 ባሉት በጀት ዓመታት በአማካይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት 7.1 በመቶ ደርሷል። በዚህም ሀገራችን በአፍሪካ ኢኮኖሚ ምኅዳር ጉልህ ሚና ያላት ሀገር ለመሆን በቅታለች። ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ያላትን ቁርጠኝነትም አሳይታለች። ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን ኢኮኖሚ ገንብታለች። ከሰሐራ በታች ካሉ አፍሪካ ሀገራት የሦስተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤትም ሆናለች። መንግሥት የግብር ገቢ የመሰብሰብ ዐቅሙ ተሻሽሏል።
 
በቅርቡ የጸደቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ቀሪ የማክሮ ኢኖኮሚ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው።
 
ይህ ፕሮግራም በአራት ምሦሦዎች ላይ የተገነባ ነው፡-
 
(1) የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊ እና ጤናማ የማከሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት፤
 
(2) ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣
 
(3) የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዐቅምን ማጠናከር እና
 
(4) ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን ዐቅም ማሳደግ ናቸው።
 
የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳችን ለጠንካራ፣ በግሉ ዘርፍ ለሚመራ፣ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት ይሆናል። ፕሮግራሙ በሚተገበርበት ወቅት ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ነጠላ አሐዝ የዋጋ ግሽበት ይኖራል ተብሎ ግብ ተጥሏል። የውጭ ምንዛሪ መዛባትን በማስተካከል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የታከስ ገቢን በማሳደግ፣ የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ውጤማነት በማሻሻል፣ የመንግሥት ዕዳ ዛላቂነትን በማረጋገጥ፣ የባንክ ዘርፍን ተወዳዳሪነትና ጤናማነት በማጎልበት እና የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ለመገንባት ትልቅ ሀገራዊ ግብ ተጥሏል።
 
ባለፉት ዓመታት፣ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራማችን ትግበራ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ጥረቶችና ድርድሮች ሲደረጉ ቆይተዋል። ድርድሮቹ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ እና የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆኑን ለማረጋገጥ በዕውቀትና በብስለት እንዲመሩ ተደርገዋል።
 
በዚህም መንግሥት ባስቀመጣቸው ዋና ዋና የማከሮ ኢኮኖሚ ዓላማዎችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ቅደም ተከተል መሠረት ስምምነት ላይ ለመድረስ ተችሏል።
 
ይህ የማከሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንከ እና በሌሎች ወሳኝ የልማት አጋሮቻችን የሚደገፍ ነው። የተመሠረተውም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራማችን እና በመካከለኛው ዘመን የኢንቨስትመንትና የልማት ዕቅዳችን ላይ ነው።
 
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ቁልፍ ዓላማዎችና ግቦች፡-
 
(1) የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል እና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለት ችግሮችን መፍታት፣
 
(2) የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስ፣
 
(3) የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት እና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ ዐቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል መፍጠር፣
 
(4) የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነት፣ ተወዳዳሪነትና ጤናማነት ማጠናከር እና
 
(5) የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፤ ጠንካራ፣ አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት ናቸው።
 
ከላይ የተዘረዘሩትን ግቦች ለማሳካት የሀገር ውስጥ ተቋማትን ማጠናከር እና የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለ ድርሻ አካላትን በፖሊሲ ማሻሻያ አተገባባሩ ላይ በማሳተፍና ግልጽነት ለመፍጠር ተችሏል። ይሄም ሀገራችን ከፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ጋር ተያይዘው የሚመጡት አዳዲስ የልማት ፋይናንስ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በአግባቡ እንድትጠቀም ያስችላታል። እንዲህ ያለ የትብብር አጋርነትና ቅንጅት ሀገራዊ የግሉ ዘርፍ የሚመራው የዕድገት አቅጣጫ እንዲሳካ ለማድረግ ለግሉ ዘርፍ መጠነ ሰፊ ዕድሎችን ይፈጥራል።
 
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ዋና ዋና እርምጃዎችና የሚጠበቁ ሀገራዊ ፋይዳዎችን በተመለከተ፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክ እና በሌሎች ወሳኝ የልማት አጋሮቻችን የሚደገፈው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራማችን ለሀገራችን ኢኮኖሚ በርካታ ጥቅሞችን እና ውጤቶችን እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።
 
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎቹ ዋና ዋና የፖሊሲ ርምጃዎችና የሚጠበቁ ሀገራዊ ፋይዳዎች የሚከተሉት ናቸው:-
በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት፦ የውጭ ምንዛሬ ግብይት በገበያው አማካኝነት እንዲበየን የማድረግ ሂደት ነው። በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማረጋገጥ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል፣ የገቢ እና የወጪ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣም ያስችላል። በክፍያ ሚዛን ላይ ያለውን አለመመጣጠንም ለማስተካከል ይረዳል። ሌሎችም ጥቅሞች አሉት።
በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት፦ ሌላኛው ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የማሻሻያ እርምጃ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን ማዘመን ነው። የሦስት ዓመት የብሔራዊ ባንከ ስትራቴጂክ ዕቅድ ዝቅተኛ እና የተረጋጋ የዋጋ ንረት መኖሩን ማረጋገጥ እንደመሆኑ መጠን፣ ባንኩ ከንግድ ባንኮች ጋር በሚያደርገው የንግድ ግብይት በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት እንዲፈጠር ቅድሚያ ይሰጣል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን የፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ ጀምሯል።
 
የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ፦ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያችን የመንግሥት ፋይናንስ ጫናዎችን እንዲቀንሱ ያደርጋል። ከላይ ከተጠቀሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ጋር ትክክለኛ የፖሊሲ መስተጋብር በመፍጠር ማከሮ ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ ያደርገዋል። የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያው ዋና ትኩረቱ የመንግሥት ገቢን ማሳደግ፤ የመንግሥት ወጪንና የድጎማ ሥርዓትን ውጤታማ ማድረግ፣ በጡረታ ፈንድ ሥርዓቶች ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን መተግበር፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ እና የመንግሥት ብድር አስተዳደር ውጤታማና አዛላቂ እንዲሆን ማረጋገጥ ናቸው። እነዚህ ርምጃዎች የበጀት አስተዳደር ውጤታማነትን እና የመንግሥት ዕዳ ተጋላጭነትን ያሻሽላሉ። በዚህ የተነሣ የልማት ፋይናንስ አማራጮቻችን ይሰፋሉ። እንዲሁም ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ ዐቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል ይፈጥራሉ።
 
የልማት ፋይናንስ ዕድሎች እና የመንግሥት ዕዳ አስታዳደር ማሻሻያ፦ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር በተደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ከተለያዩ አበዳሪዎቻችን ጋር በመነጋገር ከፍተኛ የዕዳ ማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ እየተሠራ ነው። በሌላ በኩል ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራም ኢትዮጵያ አዳዲስ የልማት ፋይናንስ አቅርቦት በተለይም ከዓለም ባንክ፣ ከሌሎች የልማት ፋይናንስ አቅራቢ ባንኮች እና ከሁለትዮሽ አበዳሪ ድርጅቶች እንድታገኝ መንገድ ይከፍታል። በዚህም መሠረት ሀገራችን በአጠቃላይ በማከሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ትግበራ መሠረት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ብዙ ቢልዮን ዶላር ታገኛለች። ይሄም የማከሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን እየጠበቁ ካሉ ከሌሎች የልማት አጋሮቻችን ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍን ለማሰባሰብም ያግዛል።
 
በመጨረሻም የማከሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙን በብቃት እና በውጤታማነት ለመተማበር መንግሥት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ከላይ የተዘርዘሩት ዋና ዋና የፖሊሲ እርምጃዎች ከአጠቃላይ ሀገራዊ የረጅምና የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅዶቻችን ጋር ተጣጥመው ይከናወናሉ። እንዲሁም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ እና የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲተገበሩ መንግሥት ከፍተኛ የክትትልና የድጋፍ ማዕቀፎችን ይዘረጋል። ለዚህም በሁሉም በሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና በመንግሥታዊ ተቋማት በኩል አስፈላጊ ከትትልና ድጋፍ ይደረጋል። በሁሉም በሚመለከታቸው ተቋማት በኩል የፖሊሲ ትግበራ አፈጻጸም ወጥነት እንዲኖር መንግሥት ጠንካራ የፖሊሲ ማሻሻያ አመራር መኖሩን ያረጋግጣል።
 
በሌላ በኩል መንግሥት እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ላሉ ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ተቋማዊ ዐቅምን ያጠናከራል። እነዚህ ተቋማት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማውጣት፣ በመተግበር እንዲሁም ተጽዕኗቸውን በመከታተልና በመገምገም ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በተመሳሳይ መልኩ መንግሥት ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ድጋፍን ለማሰባሰብ ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር ግልጽነት ያለው ግንኙነት ይፈጥራል።
 
በተጨማሪም ተጋላጭ የኅብረተሰብ ከፍሎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ። የማኅበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ድጎማ ይደረግላቸዋል። ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኞች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ሊያስከትሉ ከሚችሉት የአጭር ጊዜ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ አስፈላጊ የደሞዝ ድጎማና ማሻሻያዎች ለተወሰኑ ጊዜያት ይደረጋሉ። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን መንግስት በከፈል የሚደጉም ይሆናል። የማከሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሂደት ቀጣይነት ያለው ግምገማ ይደረግለታል። መንግሥት በወቅታዊ መረጃ ላይ በመመሥረት በፕሮግራሙ ላይ ወቅታዊ፣ አስፈላጊ እና ተገማች የፖሊሲ ማስተካከያዎችን ያደርጋል።
 
የማከሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ሂደት ተከትሎ በኢኮኖሚው ውስጥ ሊከሠት የሚችለውን የመልካም አስተዳደር ብልሹነት እና ሕገ-ወጥነት ለመከላከል መንግሥት የነቃ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ ይወስዳል። የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን በተመለከተ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች በገንዘብ ሚኒስቴርና በብሔራዊ ባንክ በኩል በየጊዜው የሚገለጡ ይሆናል።
 
ሐምሌ 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top