ልበ ቀናው የልብ መድኃኒት - ዶክተር በላይ አበጋዝ

1 Mon Ago 541
ልበ ቀናው የልብ መድኃኒት - ዶክተር በላይ አበጋዝ

ብዙዎች የማይሳካላቸውን ከራስ አልፎ ለወገን የሚተርፍ ሥራ ሠርተው ስማቸው ሲወሳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው። ለዚህ ስኬታቸው ምክንያቱ ደግሞ ከምንም በፊት ሀገር እና ወገንን ማስቀደማቸው እና ቅን አገልጋይነታቸው ነው፡፡

በተግባር የተፈተነ የሀገር ፍቅር ያላቸው እኚህ ቅን የኢትዮጵያ ልጅ በአንድ ወቅት ‘ኢትዮጵያዊ መሆን ሱዳናዊ፣ ኬንያዊ፣ አሜሪካዊ … ከመሆን ምን የተለየ ስሜት አለው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ "እኔ ምን አውቄ ሱዳናዊ ወይም ከእነዚህ የአንዱ ሀገር ዜጋ ሆኜ አላውቅ፤ ኢትዮጵያዊ ሆኜ ነው የተፈጠርኩት፤ ኢትዮጵያዊ ሆኜ መሞትም ነው የምፈልገው፤ በሕይወቴ የማልክዳቸው ሦስት ለራሴ የገባኋቸው ቃል ኪዳኖች አሉ፤ ከእነሱ አንዷ ሀገሬ ናት" በማለት መመለሳቸውን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን እምነት ሲገልጹም፣ "ልክ በሃይማኖት ሳንከራከር እንደምናምነው ኢትዮጵያዊነትንም ሳልከራከር ነው የምቀበለው፤ ምንም ቢሆን ይህንን ተስፋዬን ማጣትም አልፈልግም፤ ገንዘቤ ሊወሰድ ይችላል፤ ጤንነቴ ሊጓደል ይችላል፤ ተስፋዬን መነጠቅ ግን በፍፁም አልሻም" ይላሉ።

የሚያውቁአቸው ሰዎች "ራስ ወዳድ ያልሆኑ ቁሳቁስን ለማጋበስ ፍላጎት የሌላቸው ሀገራቸውን፣ ሕዝባቸውን እና የሰው ልጆችን የልብ ሕመም ለማከም ራሳቸውን የሰጡ እውነተኛ ሐኪም ናቸው" በማለት ምስክርነታቸውን ይሰጧቸዋል፡፡

ዶክተር በላይ አበጋዝ ህዳር 13 ቀን 1937 ዓ.ም በቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር ኩታበር ደሴ ውስጥ ነበር የተወለዱት፡፡  

የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በርካታ ስመጥር ኢትዮጵያውያንን ባፈራው ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ነው፡፡ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ዩኒቨርሲቲ ገብተው አጠቃላይ ህክምናን አጥንተዋል።

በሕክምና ሥራቸው ባዩት አጋጣሚ ነበር የልብ ሕክምናን በተለይም የሕፃናት ልብ ሕክምናን ለማጥናት የወሰኑት።  ለዚህ ውሳኔያቸው ምክንያታቸውንም ሲናገሩም "በየዓመቱ ከ50 ሺህ በላይ ህፃናት ከልብ በሽታ ጋር ይወለዳሉ፤ በተጨማሪ ከ50 እስከ 60 ሺህ ደግሞ ከተወለዱ በኋላ የልብ በሽተኛ ይሆናሉ፤ ሕክምናውን ስለማያገኙ ደግሞ ይሞታሉ፤ ለዚህ ደግሞ የግድ መፍትሄ ሊገኝለት ይገባል" ይላሉ።

ውሳኔያቸውን በተግባር ለውጠውም በሕጻናት ልብ ህክምና ስፔሻላይዝድ አደረጉ፡፡ ዶክተር በላይ ከ1973 ዓ.ም ጀምረው ላለፉት 43 ዓመታት በሕጻናት ልብ ሕክምና እና በሕጻናት ካርዲዮሎጂስትነት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር አገልግለዋል፡፡

በሐረር ወታደራዊ ትምህርት ቤትም በእጩ መኮንንነት ወታደራዊ ሳይንስ ተምረው እስከ ሌተናል ኮለኔልነት ማዕረግ ደርሰዋል፡፡ በውትድርና ሙያቸው ባሳዩት የላቀ አፈጻጸምም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አራት ጊዜ ተሸልመዋል፡፡

ዶክተር በላይ ከሕክምናው በተጨማሪ የህጻናት ህክምናን በማስተማር፣ ስለ ሙያውም ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማሳተምም ይታወቃሉ፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ አካዳሚዎች ውስጥ ንቁ ተሣትፎ ያደርጉ ነበር፡፡

ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ  የአሜሪካ ፔዲያትሪክስ አካዳሚ፣ የኢንተርናሽናል ሶሳይቲ ኦፍ ሃይፐርቱንሽን ኢን ብላክስ፣ ፓን አፍረካን ሶሳይቶ ኦፍ ካርዲዮሎጂ እና የ ዘ ናሽናል ድራግ አድቫይዘሪ ቦርድ ኦፍ ኢትዮጵያ አባል ሲሆኑ የኢትዮያን ሜዲካል ጆርናል ን በአባልነት፣ በረዳት ዋና ጸሐፊነት እና በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል፡፡

ዶክተር በላይን በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በስፋት ያስተዋወቃቸው የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ድርጅት ነው። የልብ ሕመም ያለባቸው ሕጻናት ውጭ ሀገር ሄደው ለመታከም የሚያስችል ዐቅም ስለሌላቸው የሚያጋጥማቸውን ጉዳት ለመቀነስ በመላው ዓለም ዞረው የመሠረቱት ከሀገራችን ችግር ፈቺ ድርጅቶች አንዱ ነው የህጻናት ልብ ሕክምና ማዕከል፡፡ ማዕከሉን ለመክፈት ያላሰለሰ ጥረት አድርገውም ራዕያቸውን አሳክተዋል፡፡

ዶክተር በላይ ስለ ማዕከሉ አመሰራረት ሲገልጹም፣ "በኢትዮጵያ የልብ ህክምና ማዕከል የማቋቋም ሀሳብ የተጠነሰሰው በ1970 ዓ.ም በአሜሪካ ነው፤ በልብ ህክምና ሙያ ለመሰልጠን (ስፔሻላይዝድ ለማድረግ) በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቅኩበትን የትምህርት ማስረጃ አና የወደ ፊት ፍላጎቴን የሚገልጽ ሀሳብ ለኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ አቀረብኩ፤ ቃለ-መጠይቅ ያደረገችልኝ ፕሮፌሰር ኢጂኒ ዶይል፤ ‘የምንቀበለው 10 ሰዎችን ነው፤ አንተ የተቀመጥኸው 10ኛ ላይ ነው፤ ባቀረብከው ማመልከቻ ውስጥ ጥሩ እና ደስ የሚሉ ነገሮች አይቻለሁ፤ ስላቀድካቸው ነገሮች ከአንደበትህ መስማት እፈልጋለሁ፤ እውነት ትምህርትህን ስትጨርስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ በልብ ህክምና ትሰራለህ?’ በማለት ስትጠይቀኝ፡፡ እኔም “አዎ!” በማለት በእርግጠኝነት መለስኩላት" ይላሉ፡፡

"ፕሮፌሰሯም፣ ‘ኢትዮጵያ ተመልሰህ የልብ ሆስፒታል በሌለበት፣ መሳሪያ በሌለበት፣ ባለሙያ በሌለበት፣ እንዴት ነው የልብ ሕክምና እሰራለሁ የምትለው?’ በማለት ደግማ ስትጠይቀኝ፣ ‘መላ እፈልጋለሁ’ አልኳት" ይላሉ፡፡

"ቤት ስመለስ ፊቴ ላይ የመከፋት እና የሀዘን ስሜት ያየችው ባለቤቴ፣ ‘ምነው ተከፋህ? አልተቀበሉህም እንዴ?’ በማለት ጠየቀችኝ፤ መቀበሉንስ ተቀብለውኛል፤ ነገር ግን አራት ነገሮች አርግዤ መጣሁ" አልኳት።

ሀሳባቸውን የያዙአቸው አራት ነገሮችም የልብ ሆስፒታል መገንባት፣ ውድና ልዩ የሆኑትን የልብ ህክምና መሳሪያዎች ማሟላት፣ የሰው ኃይል (ካርዲዮሎጂስት) ማፍራት እና ሆስፒታሉ በገንዘብ አቅም ዘላቂ እና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ዶክተር በላይ አበጋዝ የሰነቁት ራዕይ ጊዜው ሲደርስ እርሳቸው የማስተባበር አቅም እና በተባባሪ አካላት ጥረት እውን ሆነ፡፡ ማዕከሉ በ2001 ዓ.ም ተጠናቅቆ ተመረቀ፡፡ ዘመናዊ የልብ ቀዶ ህክምና መሣሪያዎች "ቼይን ኦፍ ሆፕ ዩኬ" በሚባል ድርጅት ተሟላ፡፡ የልብ ቀዶ ሀኪሞች (ካርዲዮሎጂስቶች) ደግሞ የሚኒያፖሊስ የልብ ቀዶ ሐኪም በሆኑት በዶክር ቪብ ክሸንት እና ታዋቂ በሆነው የህንድ ናርያና ሆስፒታል ሰልጥነው ዝግጁ ሆኑ፡፡

የማዕከሉ ምሥረታ እውን እንዲሆን "አንድ ብር ለአንድ ልብ" በሚል ሃሳብ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ተሳታፊ ማድረግ የቻሉበት አካሄድም የሚታወስ ነው። የዶክተር በላይን በጎ ዓላማ የተረዱት 100 የሚጠጉ በጎ ፍቃደኞች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መረጃውን በማሰራጨት በኩል በብዙ ተሳትፈዋል።

ዶክተር በላይ ለበርካታ ዓመታት ደከመኝ ሠለቸኝ ሳይሉ፣ በወቅቱ የሚያጋጥሙአቸው መስናክሎች እና ችግሮች ሳይበግሯቸው፣ ለሀገራቸው በሕክምናው ዘርፍ የማይረሳ አሻራ ጥለዋል፡፡

በዚህ በጎ ተግባራቸውም በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት የልብ የሕክምና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችለዋል። ለአንድ ሕፃን ሕክምና ያስፈልግ የነበረውን የ30 ሺህ ዶላር ወጪ፣ የጊዜ ብክነት፣ የወላጆችን እንግልት እና ስቃይ በማስቀረት እውነተኛ የልብ መድኃኒትነታቸውን አስመስክረዋል።

ከ15 ዓመት በፊት የተቋቋመው የሕፃናት የልብ ሕክምና ማዕከል ከባድ ሊባሉ የሚችሉ የልብ ቀዶ ጥገናዎችን በሀገር ውስጥ በኢትዮጵያውያን ሐኪሞች መስጠት መቻሉ ትልቅ ተስፋ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር በላይ፣ ይሁን እንጂ በአላቂ ዕቃዎች እጥረት የተነሳ ማዕከሉ የተሟላ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ እንደሚያስቆጫቸው ይናገራሉ። 

ሮጠው ያልጠገቡ የሀገር ተስፋ ህጻናት በአላቂ ዕቃዎች እጥረት ምክንያት ሕክምና በማጣት እንዳይቀጩብን መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ፣ ማዕከሉ ተጠናክሮ ለብዙዎች እንዲደርስ ደግሞ ህብረተሰቡ ከጎኑ እንዲቆም እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡

ማዕከሉ በአላቂ እቃዎች እጥረት ምክንያት እክል ባይገጥመው በዓመት ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ህጻናት አገልግሎት ሊሰጥ ይችል እንደነበር እና ለብዙዎች እፎይታ እንደነበር  ይነገራል፡፡

ዶክተር በላይ ከልብ ሕክምና ማዕከሉ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም የሚያስተምር፣ ጥናት የሚያደርግ የልብ ሕክምና ኮሌጅ እንዲመሰረት ከማድረጋቸው ባሻገር በሚያስፈልጉት እገዛዎች የተለያዩ ግለሰቦች፣ ሀገራትን እና ተቋማትን በማናገር የሕክምና ኮሌጁ በሁለት እግሩ ቆሞ ለኢትዮጵያ ሕፃናት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከፍተኛ ሚና ተወጥተዋል።

በዚህ ቀናነታቸው እና ባስገኙት ውጤትም ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጭ በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በ2008 ዓ.ም በልብ ህክምና ዘርፍ ባደረጉት በጎ አስተዋጽኦ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማአረግ ተቀብለዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ነበሩ፤ የልብ ሕሙማን ሕክምና መርጃ ማኅበር ምስረታ 30ኛ ዓመት ሲከበርም ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅ የሕይወት ዘመን አገልግሎት ዕውቅና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።  

ልብን ለልብ ማስገዛት ልባዊነትን ይጠይቃል፤ ልብን በልብ መተካት ልበኛነትን ይታጠቃል፤ ልብን በልብ ለማዳንም አዋቂ ልብን ያስናፍቃል፡፡

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top