የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በ424 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበረውን ሁለተኛው ዙር የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
ኘሮጀክቱ በ7 ክልሎለች እና ድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ 120 ወረዳዎች የሚተገበር ነው።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የፕሮጀክቱ ዓላማ በሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ሕይወት ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ማጠናከር ነው።
ኘሮጀክቱ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች ፣ እንሰሳት ጤና ፣መኖ ልማት እንዲሁም አማራጭ የገቢ ምንጭ መፍጠር ላይ የሚሰራ ሲሆን፤ 3 ሚሊዮን አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶአደር ማህበረሰብን ተጠቃሚ ያደርጋል።
2 ሚሊዮን የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
በፕሮጀክቱ ከ30 እስከ 50 በመቶ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም ተጠቁሟል።
ኘሮጀክቱ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ይተገበራል፤ በማስጀመሪያ ሥነ-ሥረዓቱ ላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፤ የልማት አጋሮች እና የሚመለከታቸው ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።