ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በሀዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራን አስጀመሩ

8 Mons Ago 863
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በሀዋሳ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራን አስጀመሩ

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በሃዋሳ ከተማ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት የሚከናወን የኮሪደር ልማት ስራን አስጀምረዋል።

የኮሪደር ልማቱ በሁለት ምዕራፍ ተከፋፍሎ የሚሰራ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ 12.6 ኪ.ሜ የሚሽፍን የሦስት መንገዶች ልማት ይከናወናል ተብሏል።

መንገዶቹ ከሜንቦ መብራት እስከ ሪፈራል አደባባይ፤ ከሻፌታ አደባባይ እስከ ሳውዝ ስፕሪንግ እና ከዲ.ኤም.ሲ እስከ ታቦር ሴራሚክ ያሉት ናቸው።

መንገዶቹ የአረንጓዴ ልማት፣ የእግረኛ መንገድ፣ የማረፊያ ስፍራዎች፣ የብስክሌት መንገድ፣ የማስ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና ደረጃቸውን የጠበቁ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶችን ያካተቱ ናቸው ተብሏል።

በሌላ በኩል በሁለተኛው ምዕራፍ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች 35 ኪ.ሜ የሚሸፍን የ10 መንገዶች ከፈታ ለማከናወን ታቅዷል።

መንገጆቹ ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ስራዎች አመቺ እንዲሆኑ ከ30 እስከ 50 ሜትር ስፋት ይኖራቸዋልም ነው የተባለው።

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ፕሮጀክቶቹ የሐዋሳ ከተማን ደረጃ በማሻሻል ለኑሮ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በልማት ዙሪያ ላይ የሚያደርገውን ቀና ትብብር እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።

የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ መኩሪያ ማርሻዬ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቶቹ አጠቃላይ ወጪ በመንግሥት፣ በህብረተሰቡ እና በባለሃብቶች ተሳትፎ የሚሸፈን ነው ተብሏል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የተያዙ ዕቅዶችን በቀጣዮቹ 3 ወራት ጊዜ ውሰጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል።

በሚካኤል ገዙ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top