ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ተግባር መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ

6 Days Ago
ኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ተግባር መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ
1445ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል። በዓሉን ምክንያት በማድረግም በአዲስ አበባ ስታዲዮምና በዙሪያው እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ አና በሌሎች ክፍለ ከተሞች ላይ በሚገኙ መስጂዶች ለሚከናወነው የኢድ ሶላት ስነ-ስርዓት የፀጥታ አካላት ለሚያከናውኑት የፀጥታ ስራ ምዕመናኑ ተባባሪ እንዲሆን ግብረ-ሐይሉ ያስታወቀ ሲሆን የሶላት ስነ-ስርዓት ያለ ምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከናወን ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
 
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ለበዓሉ ሰላማዊነት የፀጥታ ኃይሉን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በአዲስ አበባ ፖሊስ የተደረገውን ውይይት በመሩበት መድረክ ላይ ህብረተሰቡና የፀጥታ ኃይሉ በቅንጅት በመስራታቸው ከዚህ ቀደም ህዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት ያከበራቸው ልዩ ልዩ በዓላት በሰላም መከበራቸውን በማስታወስ እንደ ከዚህ ቀደሙ የህዝቡን አቅም በተገቢው መጠቀም እንደሚገባ ተገልጿል።
 
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በሰጡት የሥራ መመሪያ ህዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት የሚያከብራቸው በዓላት ለሀገር ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
 
የሀገራችን ሰላም መሆን እንቅልፍ የሚነሳቸውንና በህብረተሰቡ ውስጥ ተመሳስለው የሚገኙትን ፀረ-ሰላም ኃይሎች የመመንጠሩ ስራ እንዲሁም በዘረፋ፣ በሌብነት እና በሌሎች ወንጀሎች ላይ የተሰማሩ ሕገ-ወጦች ላይ የተጀመረው ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ አስታውቀዋል። በዓሉ በሰላም እንዲከበር ሁሉም በተሰማራበት የፀጥታ ስራ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥብቅ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
 
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው መላው የከተማችን ነዋሪዎች የፀጥታውን ስራ በመደገፍ በኩል እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል። ወ/ሮ ሊዲያ አክለውም የሰላም ሰራዊት አባላት ለከተማችን ሰላም እየተወጡት ያለውን ድርሻ በማጎልበት ለበዓሉ ሰላማዊነት ከፀጥታ አካሉ ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ አቅጣጫ ተሰጥቷል ብለዋል።
 
በያዝነው ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞች እንዲሁም ህዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት ያከበራቸው ኃይማኖታዊ፣ ብሔራዊ በዓላት ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መከበራቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አስታውሰዋል።
 
የእነዚህ ሁነቶች በሰላም መጠናቀቅ ዋነኛው ምክንያት የፀጥታው ኃይሉ ከሰላም ወዳዱ ህብረተሰብ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ የተገኘ ውጤት እንደሆነም ኮሚሽነር ጌቱ ጠቅሰዋል። ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመስራታችን አብይት ሁነቶች በሰላም እንዲከበሩ ከማስቻሉ ባሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና አጥፊዎችን ሕግ ፊት ለማቀርብ እያገዘን ስለሆነ የህብረተሰቡ እና የፀጥታ አካላት ጥምረት እንዲጎለብት ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።
 
1445ኛው የኢድል አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን የተናገሩት ኮሚሽነር ጌቱ፤ በተለይ በአዲስ አበባ ስታዲዮም እና በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚከናወነው የሰላት ስነ-ስርዓት ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ለእምነቱ ተከታዮች በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን ሁለቱም ከፍተኛ አመራሮች በፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ስም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
 
በአዲስ አበባ ስታዲዮምና በልዩ ልዩ መስጂዶች ከሚደረገው የሰላት ስነ-ስርዓት በተጨማሪ በተለያዩ በክፍለ ከተሞች ለሚከናወነው የኢድ ሶላት የሚመጡ ምዕመናን ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ ስለሚኖር ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ የተለመደ ትብብሩ እንዲያደርግ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል መልዕክቱን አስተላልፏል።
 
ለስራው ስኬታማነት ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ትብብር ግብረ ኃይሉ ምስጋናውን አቅርቦ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት በጀመረው በዜጎች መረጃ መቀበያ (EFPAPP) ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመጠቀም ጥቆማዎችን በፍጥነት በመስጠት ወይም በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች መረጃውን በአካል በማድረስ የተለመደትብብራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን እያቀረበ በድጋሜ በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆንላችሁ መልካም ምኞቱን ይገልፃል።
 
ዒድ ሙባረክ!
የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል
ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top