36 በመቶውን የመድሃኒትና የሕክምና ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ተችሏል፡- ዶክተር መቅደስ ዳባ

7 Days Ago
36 በመቶውን የመድሃኒትና የሕክምና ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ተችሏል፡- ዶክተር መቅደስ ዳባ
በኢትዮጵያ አሁን ላይ 36 በመቶውን የመድሃኒትና የሕክምና ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን መቻሉን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
 
የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
 
በመድረኩ ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የጤና ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል።
 
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅዳስ ዳባ፤ በመቶ ቀናት የግምገማ መድረክ የተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮችን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
የጤና ተቋማትን በማዘመን፣ አገልግሎታቸውን በማሳደግ እንዲሁም ተጨማሪ ግንባታ በማድረግ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
 
በመሆኑም በእናቶች፣ በህፃናትና ጨቅላ ህፃናት ህክምና አገልግሎት ዙሪያ የነበሩ ችግሮችን በማቃለል የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመድሃኒትና ሌሎች የህክምና ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመጠቀም ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ መቻሉንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
 
የመድሃኒትና የህክምና ግብአቶች የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ 8 በመቶ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ 36 በመቶ የሚሆነውን የመድሃኒትና የህክምና ግብአት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ተችሏል ብለዋል።
 
የሀገር ወስጥ አምራቾች እንዲበረታቱና አዳዲስ ኢንቨስተሮች በዘርፉ እንዲሰማሩ መደረጉ ለስኬቱ ቁልፍ ክንውኖች መሆናቸውን ጠቅሰው ባለፉት መቶ ቀናት ብቻ ሁለት አዳዲስ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ሀገር ውስጥ ገብተው ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
 
በመድሃኒት ልማትና አቅርቦት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ ለአህጉራዊ ተደራሽነት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
 
ሊዚህ ይረዳ ዘንድ የቁጥጥር አቅምን ማሻሻል፣የክትባት ምርት ለመጀመርና የዘርፉን ልማት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
የበሽታ በተለይም የወረርሽኞችን የመከላከል አቅም በማሳደግ በርካታ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ወባን ጨምሮ ሌሎች የጤና ስጋቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top