ተጨማሪ የጃፓን ባለሐብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ገልፀዋል።
አምባሳደሩ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ጋር ተወያይተዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያና ጃፓን ካላቸው ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት አንፃር የጃፓን ኢንቨስተሮች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ከምንግዜውም በላቀ መልኩ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም በኢንዱስትሪ ፓርኮች እያመረቱ የሚገኙ ዓለም ዓቀፍ እና ሀገር በቀል ኩባንያዎች አሁን ላይ ካላቸው ገበያ በተጨማሪ የጃፓንን ሰፊ የገበያ አቅም መጠቀም በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ምክክር ተደርጓል።
አምባሳደሩ በበኩላቸው፤ በቅርቡ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፓስፖርትን ጨምሮ ዓለም ዓቀፍ የደኅንነት መስፈርቶችን የሚያሟሉ ምስጢራዊ የሕትመት ውጤቶችን የሚያመርት ቶፓን ግራቪቲ የተሰኘ ግዙፍ የጃፓን ኩባንያ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን አስታውሰዋል፡፡
ተጨማሪ የጃፓን ባለሀብቶችም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን አምባሳደሩ መግለጻቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡