የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለጋምቤላ ክልል የህዝብ ቤተ መፅሀፍት የተለያዩ መጽሐፍትን አበረከተ

7 Mons Ago 613
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ለጋምቤላ ክልል የህዝብ ቤተ መፅሀፍት የተለያዩ መጽሐፍትን አበረከተ

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን "የመጽሐፍት ቤተኛ" በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የመቶ ቀናት የንባብ ዘመቻ ማጠቃለያ ላይ ያስተላለፉትን ጥሪ ተቀብሎ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

በዚህም መሰረት በቀጣይ ዓመት የሚከበረውን 60ኛውን የቴሌቪዥን ምስረታ በማስመልከት "የኢቢሲ ስጦታ ለ60 ዓመታት 6 ሺህ መጽሐፍት" በሚል መሪ ቃል ለሁሉም ክልሎች የህዝብ ቤተ መጸሐፍት፣ ለህጻናት እና ታዳጊዎች የክረምት የንባብ ጊዜ የሚሆኑ መጽሐፍትን እያበረከተ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በጋምቤላ ክልል ለህዝብ ቤተ መጽሐፍት ያበረከተው ስጦታም የዚሁ መርሐግብር አንዱ አካል መሆኑም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የአቅርቦት ዲቪዥን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን ቲማ መጽሐፍቱን ለክልሉ ባስረከቡበት ወቅት ኮርፖሬሽኑ በቀጣዩ ዓመት የሚያከብረውን የቴሌቪዥን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት 6 ሺህ መጽሐፍትን በማሰባሰብ ለህዝብ ቤተ መጽሐፍት ለማከፋፈል የያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሚድያው ዘርፍ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እና የማህበረሰቡን የንባብ ባህል ለማዳበር የድርሻውን በማበርከት ላይ እንደሚገኝም አቶ ጌታሁን ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ አቶ ፒተር አማን በርክክብ መርሐግብሩ ላይ እንዳሉት ኮርፖሬሽኑ የማህበረሰቡን የንባብ ባህል ለማጎልበት ለክልሉ ላበረከተው የመጽሐፍት ድጋፍ አመስግነዋል።

ኢቢሲ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ሊያጠናክር እንደሚገባም አቶ ፒተር ገልፀዋል።

የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ሰሞኑን የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 24ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በተከበረበት ወቅት በገለፁት መሰረት አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የማህበረሰቡን የንባብ ባህል ለማጎልበት የሚያግዙ የተለያዩ መጽሐፍትን በማሰባሰብ ለአንባቢያን ተደራሽ የማድረጉን ተግባር ዛሬ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ ጀምሯል።

በሚፍታህ አብዱልቃድር


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top