#አውደሰብ - የመጀመሪያውን የአማርኛ ታይፕራይተር የፈጠሩት ኢንጅነር አያና ብሩ

7 Mons Ago 1899
#አውደሰብ - የመጀመሪያውን የአማርኛ ታይፕራይተር የፈጠሩት ኢንጅነር አያና ብሩ

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የቆየው ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ (STRIDE Ethiopia 2024 Expo) በተለያዩ ዘርፎች የሕይወት ዘመን ሽልማቶች በመስጠት ተጠናቋል።

በሕይወት ዘመን አበርክቶ ሽልማት ምድብ በየዘርፉ ለሀገራቸው ዘመን ተሻጋሪ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን የሕይወት ዘመን ሽልማቶች ተሰጥቷል። ተሸላሚ ከነበሩት ግለሰቦች መካከልም፡- ዛሬ ታሪካቸውን በአጭሩ የምናቀርበው እና በዚህ መድረክ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ኢንጂነር አያና ብሩ ናቸው።

ኢንጂነር አያና ብሩ የመጀመሪያውን የአማርኛ ታይፕራይተር የሠሩ በመሆናቸው  “የኢትዮጵያ ታይፖግራፊ አባት” በሚል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሕይወት ዘመን ሽልማት ሰጥቷቸዋል። ለመሆኑ ኢንጂነር አያና ብሩ ማን ናቸው?

ኢንጅነር አያና ብሩ ትውልድ እና እድገታቸው በወለጋ ነው። በወቅቱ በእንግሊዝ ኤምባሲ ሲሠሩ የነበሩት ታላቅ ወንድማቸው አቶ ዳባ ብሩ አያናን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ዳግማዊ ምንልክ ትምህርት ቤት አስገቧቸው። የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በብቃት ያጠናቀቁት አያና ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ግብፅ ተላኩ። ከዚያም ወደ እንግሊዝ ሀገር በማቅናት ከለንደን ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና ተመርቀዋል። እንግሊዝ ሀገር እያሉም ለሀገራቸው የሚጠቅም ሥራ ሲያልሙ የነበሩት ኢንጂነር አያና “ኦሊቬቲ” ከተባለ የጣሊያን ካምፓኒ ጋር ባደረጉት ምርምር የመጀመሪያውን የአማርኛ ታይፕራይተር ማሽን ዲዛይን አዘጋጁ።

 ይህን ዲዛይን ወደ ተግባር ለመቀየር አንግሊዝ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች ለማስተዋወቅ ቢሞክሩም "የአማርኛ ፊደል(ቋንቋ) የሚያገለግለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ በመሆኑና ገበያ ስለማያስገኝ አያዋጣንም" የሚል ምላሽ ተሰጣቸው። በምላሹ ተስፋ ያልቆረጡት ወጣቱ መሐንዲስ ዲዛይኑን ይዘው ወደ አሜሪካኖች ሲሄዱ አሜሪካኖቹ እንደሚሠሩላቸው ግን የአሜሪካ አርማ እንደሚታተምበት ነገሯቸው፤ ኢንጂነር አያናም በሥራቸው ላይ የኢትዮጵያ አርማ እንዲታተም ፍላጎት ቢኖራቸውም አማራጭ ስላልነበራቸው ፈቅደው ሁለት ታይፕራይተሮችን አሠርተው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።ማሽኑን ለንጉሡ በመስጠትም አገልግሎት ላይ እንዲውል አድርገዋል።

ግንቦት 1939 ዓ.ም የጽሑፍ መኪናዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ተፈቅዳ ጽሑፍ ታትሞበታል። ኢንጅነሩ የሠሯት የመጀመሪያዋ የአማርኛ ታይፕራይተርም በብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ትገኛለች። 

ኢንጂነር አያና በዘመናቸው በዓለም ላይ የነበረው የፈጠራ ሥራ ለሀገራቸው ጥቅም እንዲውል ያደረጉ ትውልድ እና ዘመን ተሻጋሪ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ይህም ለሳቸው ዘመን እና ከዚያ በኋላ ለመጣው ትውልድም በሙያ ሀገርን ማገልገል ምን እንደሆነ ያሳዩበት ከመሆኑም ባሻገር ለዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር መሰረት የጣለ ነው።

በመቀጠልም በአውራ ጎዳና ኃላፊነት ተመድበው መሥራት ጀመሩ። በዚያ ሲያገለግሉም ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚወስደውን መንገድ እያጠናቀቁ እያሉ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ሀገራችንን ለመውረር እየገፋች መጣች። ከዚያም ሥራውን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው ወደ ማይጨው በመዝመት ከጠላት ጋር ተዋግተዋል። በማይጨው የነበረው የወገን ጦር ሲፈታም ወደ መሀል ሀገር በመመለስ የሽምቅ ውጊያን ማስተባበር ጀመሩ። ንጉሡ ወደ ውጭ እንዲሄዱ ሲወሰንም ኢንጂነር አያናን አስጠርተው እሳቸው እንግሊዝኛ ቋንቋን ስለሚችሉ አብሯቸው እንዲሄዱ ጠይቋቸው ነበር፤ ኢንጂነር አያና ግን የንጉሡ መሄድ አስፈላጊ ከሆነ አርበኞቹን የሚያስተባብር አንድ ሁነኛ ሰው ትተው እንዲሄዱ፣ በሳቸው በኩል ግን ወደ ውጭ ከመሄድ እዚሁ ሀገር ውስጥ ሆነው አርበኞቹን ቢስተባብሩ እንደሚመርጡ ተናግረው እዚሁ ቀሩ።

ጣሊያን አዲስ አበባን ሲቆጣጠርም ኢትዮጵያ የጣሊያንን አገዛዝ እንዳልተቀበለች የሚያጋልጡ መልዕክቶችን በማዘጋጀት ማሰራጨት እና ለአርበኞች መረጃን የማቀበል ሥራቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ግራዚያንን ለመግደል የተደረገውን ሙከራ በማቀናበር የተጠረጠሩት ኢንጅነር አያና፣ ጣሊያኖች በግራዚያኒ አማካኝነት፣ "አያናን አንገቱን ቆርጦ ለሚያመጣልን አሥር ሺህ ጠገራ እንከፍላለን" የሚል አዋጅ አስነገረች። ኢንጂነር አያና ግን ምንም ሳይፈሩ ወራሪውን መታገላቸውን ቀጠሉ።

በኋላም ወደ ጊምቢ ወለጋ ሄደው ህዝቡን እየቀሰቀሱ አርበኞችን እያበረታቱ ቢዚያው ወደ ሱዳን ተሻገሩ። በሱዳንም ከንጉሡ እየተጻጻፉ የማበረታቻ መልዕክቶችን ለአርበኞች ማድረሳቸውን ቀጠሉ። የጣሊያንን ግፍ ሲቃወሙ ከነበሩት ሲልቪያ ፓንክረስት ጋርም ተገናኝተው የጣሊያንን ግፍ በጋዜጦች በማሳተም ለዓለም ማኅበረሰብ ማጋለጣቸውን ቀጠሉ። ወደ ጊምቢ በመመለስ አርበኞችን በመቀስቀስ ላይ እያሉ አንዱ አብሮ አደግ ወዳጃው ወደ ቤቱ ወስዶ ከደበቃቸው በኋላ በጎን ለጠላት ጠቁሞ አስያዛቸው፤ ጠላትም በጊምቢ ከተማ ገበያ ላይ በጥይት ደብድቦ ገደላቸው።

ሀገርን ማገልገል ልማዳቸው የሆነው ኢንጂነር አያና ቤተሰብ፤ ልጃቸው ኮሎኔል አበራ አያና በደርግ ዘመነ መንግሠት የአዲስ አበባ ፖሊሰ ዋና አዛዥ ሆነው ሠርተዋል። ኮሎኔል አበራ በኃላፊነት ባገለገሉበት ወቅት የማረሚያ ቤት ሥርዓቶችን እና የህግ ታራሚዎችን አያያዝ የቀየሩ ታላቅ ሰው እንደነበሩ ታሪካቸው ያሳያል። አንድ በህግ ጥላ ስር ያለ ሰው የማረሚያ ጊዜውን አጠናቆ ወደ ሕብረተሰቡ ሲመለስ በአዕምሮም፣ በአካልም፣ በክህሎትም ጎልብቶ ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆን የተለያዩ ሙያዎች ሥልጠና እና የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴዎች በወህኒ ቤቶች ውስጥ ተጠናክሮ እንዲሰጥ ያደረጉ ናቸው።

በዛሬ ዕለት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሳይንስ ሙዝየም ሲካሄድ የቆየው ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ (STRIDE Ethiopia 2024 Expo) ማጠቃለያ ላይ በተለያዩ ዘርፎች የህይወት ዘመን ተሸላሚዎች ከነበሩት ግለሰቦች መካከልም አበራ ሞላ (ዶ/ር) የግዕዝ ፊደላት በመደበኛ ደረጃ ከኮምፒውተር እንዲተዋወቅ በማድረግ የግዕዝ ፊደላን በኮምፒውተር ማቀናበር እንዲቻል መሠረት የጣሉ ናቸው።  ዘመኑን የዋጀ ሥራ የሠሩት ታላቅ ሰው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የህይወት ዘመን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ሌላኛው ተሸላሚ አቶ ዳንኤል መብራቱ የዳን ቴክኖክራፍት እና የዳን ሊፍት መስራች እና ባለቤት ናቸው። አቶ ዳንኤል ዳን ቴክኖ ክራፍትን በመመሠረት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ በሀገራችን ሊፍት እንዲመረት ላደረጉት አስተዋጽኦ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የህይዎት ዘመን ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

በለሚ ታደሰ

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top