በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው

7 Mons Ago 698
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት  የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ  ነው
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
 
መድረኩ መቻቻልን በማዳበር ችግሮችን በጋራ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
 
በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
 
በዚህ ወቅት አቶ አረጋ ከበደ፤ በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግባቸው የሚወክሉትን ህዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል ሰላማዊ ትግል ማካሄድ እንደሆነ ተናግረዋል።
 
የጋራ ምክር ቤቱ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትን የሰመረ በማድረግ ለህዝብ ጥቅም በጋራ መስራትን የሚያጎለብት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
 
በምክር ቤቱ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመንግስት በማቅረብና የሚፈቱበትን ስልት በመዘየድ የፓርቲ ና የመንግስት ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል በመሆኑ ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
 
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ከ2013 ዓ. ም ጀምሮ የፖለቲካ ልዩነታችን በመጠበቅ በዋና ዋና ክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንድንሰራ አስችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በዚህም የምክር ቤቱ አባላት በተፎካካሪነት ውስጥ በትብብር መስራትን ባህል ለማጎልበት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
 
የምክር ቤቱ መቋቋም ያለፈው ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና ሌሎችንም ተግባራት በትብብር በመስራት ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
 
መንግስት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስፈላጊነት በመገንዘብ በካቢኔና ሌሎች የአመራርነት ቦታዎች በመመደብ በጋራ ለአገር እድገት የበኩላችንን እንድንወጣ እያስቻለን መሆኑን መገንዘብ ይገባል ሲሉ አንስተዋል።
 
በክልሉም ሆነ በአገሪቱ ችግሮች በውይይት በመፍታት የሰለጠነ ፖለቲካ ስር እንዲሰድ አባል ፓርቲዎች እየሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆንም የሚጠበቅብንን ሚና በመወጣት ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የምክር ቤቱ አባላት መስራት አለብን ሲሉ አመልክተዋል።
 
በቀጣይም የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት፣ አንዱ ከሌላው ፓርቲ የሚኖረውን ግንኙነት ከአገርና ህዝብ ጥቅም አንፃር በመመዘን የተሳለጠ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
 
የዛሬው የምክር ቤቱ መድረክ መቻቻልን በማዳበር ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በምክክር መድረኩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር አባላት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top