ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ 800 ቶን የጥጥ ምርት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል - የግብርና ሚኒስቴር

2 Mons Ago
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ 800 ቶን የጥጥ ምርት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል - የግብርና ሚኒስቴር

በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ 800 ቶን የጥጥ ምርት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት አመቺ ስነ-ምህዳር ቢኖራትም የምታመርተው ከእምቅ ኃብቷ ጥቂቱን ብቻ መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።

በግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሳምሶን አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለጥጥ ልማት ቆላማ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች ተመራጭ ናቸው።

ለአብነትም በሀገሪቱ የጥጥ ልማት ሥራ ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች ውስጥ በአፋር ክልል ገዋኔ፣ መተማ፣ ሑመራ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ወላይታና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተጨማሪም በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ላይም እንዲሁ ሰፋፊ የጥጥ እርሻዎች እንደሚለሙ አክለው ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ በዘንድሮው የምርት ዘመን በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በፋይናንስ አቅርቦትና በጸጥታ ችግር ሳቢያ በታሰበው ልክ የጥጥ ልማት ሥራው አልተከናወነም ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በጥጥ ልማት ለመሸፈን ከታቀደው 105 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 81 ሺህ ሄክታር መሬት መሸፈን ተችሏል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የጥጥ ምርት መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ የዕቅዱን 80 በመቶ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከዚህ ውስጥ 800 ቶን ጥጥ ለውጭ ገበያ በማቅረብ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት አመቺ ስነ-ምህዳር ቢኖራትም የምታመርተው ከእምቅ ኃብቷ ጥቂቱን ብቻ መሆኑን አቶ ሳምሶን አክለዋል።

ከአየርና ከመሬት ኃብት አኳያ 3 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ኃብት እንዳላት አብራርተዋል።

በመሆኑም ሀገሪቱ ከጥጥ ምርት ማግኘት ያለባትን ጥቅም እያገኘች ባለመሆኑ፤ ዘርፉን ለማሳደግና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ለማጉላት አዳዲስ የአሠራር ሥርዓቶች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ የ15 ዓመት ብሔራዊ የጥጥ ልማት ስትራቴጂ ዕቅድ ተነድፎ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።

ስትራቴጂው በጥጥ ልማት ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን በመለየት ብሎም የሀገራትን ልምድ በመቅሰም ኢትዮጵያ ያላትን አቅም አሟጦ መጠቀም ላይ ትኩረት ያደረጋል ይላሉ።

በተጨማሪም በዘርፉ የሚስተዋሉ የግብይት ሥርዓትን ማዘመን፣ የጥጥ ምርት ጥራትን ማስጠበቅና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ 28 የጥሬ ጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች እንዳሉ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top