ዋሽንግተን ዲ.ሲ.የሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ኤምባሲ ከዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ-አሜሪካ ቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት ፎረም በዋሽንግተን ዲሲ አካሂዷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተለያዩ የውጭ እና የውስጥ ፈተናዎች ቢገጥሟትም ኢኮኖሚው እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ አሁንም ዕድገት እያስመዘገበ ነው።
የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በመንግስት እየተተገበረ ያለው መጠነ ሰፊ የሪፎርም ስራና በመሰረተ ልማቶች ላይ በተከናወኑ ትልልቅ የኢንቨስትመንት ስራዎች መሆኑን ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም፣ በምግብ ራስን ከመቻል እንዲሁም ዘላቂ የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግና ከተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት አንጻር ትልቅ ድርሻ የሚይዘው የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል።
አሜሪካውያን ባለሀብቶች ኢትዮጵያን መጥተው እንዲጎበኙ እና ያሏትን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲያዩ ግብዣቸውን አስተላልፈዋል።
በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶክተር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያላት መሆኗን ገልጸዋል።
በተለያዩ ጊዜያት የከፍተኛ ባለስልጣናት የስራ ጉብኝቶች የተካሄዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ባለፈው ዓመት በዩ.ኤስ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳትፎ ማድረጉን አንስተዋል።
በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ አስተዳደር፣ ኮንግረስ፣ እና በግሉ ኤኮኖሚ ዘርፍ ከተሰማሩ አካላት ጋር ውጤታማ ውይይቶች ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።
በዚህ ፎረም ላይ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት እና የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሁም ኢንቨስተሮች ሊያገኙ የሚችሉትን የተለያዩ ማበረታቻዎችን አስመልክቶ ሰፊ ገለጻ ቀርቧል።
በተጨማሪም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ስኬታማ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እና የተለያዩ አሜሪካውያን የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።
ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ የተሰጠ መሆኑም በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
በፎረሙ የተሳተፉ አሜሪካውያን ባለሀብቶች፤ መንግስት እያካሄደ ያለው ሪፎርም በተለይም የውጭ ኢንቨስተሮች መዋእለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት ማድነቃቸው ተገልጿል።