"ኢትዮጵያውያን የሰላምን ዋጋ መረዳትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር ይኖርብናል" - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

1 Mon Ago 342
"ኢትዮጵያውያን የሰላምን ዋጋ መረዳትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር ይኖርብናል" - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

እኛ ኢትዮጵያውያን የሰላምን ዋጋ መረዳትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር ይኖርብናል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ይህ የተገለጸው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በባዝል ከተማ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በስዊዘርላንድ ባዝል ከተማ በተካሄደው 3ኛው ዓለም ዓቀፍ የትብብር መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ባቀኑበት ወቅት ነው በስዊዘርላንድ ነዋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይቱን ያካሄዱት።

በወቅቱም ፕሬዝዳንቷ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዳያስፖራው ከሀገሩ ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከርና ተሳትፎውንም ማሳደግ እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን የሰላምን ዋጋ መረዳትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር ይኖርብናል ያሉት ፕሬዝዳንቷ ይህ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የዳያስፖራ አባላትም በበኩላቸው ከፕሬዝዳንቷ ጋር የሚወያዩበት መድረክ በመመቻቸቱ ምስጋናቸውን ገልጸው፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን አንስተዋል።

የውይይት መድረኩን በጋራ የመሩት በጄኔቫ የኢፌዴሪ ቋሚ መልክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው በበኩላቸው፤ የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውንና ጥያቄዎችን በግልፅ በማቅረብ የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸው ተገቢና ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

የሚሲዮን ጽ/ቤቱም ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር በትብብር ለመስራትና የዳያስፖራውን ሁለገብ ተሳትፎ ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top