"ሐረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ" - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

1 Mon Ago 364
"ሐረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ" - ርዕሰ መስተዳድር  ኦርዲን በድሪ
ሐረር ከተማን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
 
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ክልሉ ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች እንዳሉትጠቅሰዋል።
 
የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጨምሮ ሌሎች የመስህብ ስፍራዎች በክልሉ እንደሚገኙ ገልጸው፤ መስህቦቹን በአግባቡ በማልማትና በመጠበቅ ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
 
በተለይ ከመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ ከተገኘው 70 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ ከመንግስት በጀት 141 ሚሊዮን ብር በመመደብ የሐረር ኢኮ ፓርክ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን አንስተዋል።
 
ፕሮጀክቱ በቀጣይ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅም፤ ጅቦችን ከመመገብ ትርዒት ባሻገር፤ ክልሉን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ጥሩ የገቢ ምንጭን እንደሚሆንም ገልጸዋል።
 
መሰረተ ልማት ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ መንግሥት በተመደበ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የአጂፕ ኢኮ ፓርክ የአስፋልት መንገድ ልማትን ጨምሮ የሐረር መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ልማት ስራዎች በአካባቢው ያለውን ተፈጥሮአዊ ስነምህዳር በመጠቀም ታሪክ፣ ባህል እና እሴትን በጠበቀ መልኩ መሰራቱን ጠቁመዋል።
 
በክልሉ የቱሪስት ልማት ሥራው የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳድሩ መግለጻቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top