የቻይና ሳይንቲስቶች የቲክ ቶክ መተግበሪያ የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ተገለጸ

2 Mons Ago 548
የቻይና ሳይንቲስቶች የቲክ ቶክ መተግበሪያ የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ተገለጸ
የቻይና የሥነ ምህዳር ተመራማሪዎች በመላው ቻይና ወረራ የሚያካሄዱ አዳዲስ የነፍሳት ዝርያዎችን ስርጭት ለመከታተል በኢንተርኔት የተለጠፉ ጽሑፎችን፣ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን እያጠኑ ነው፡፡
 
የሥነ ምህዳር ተመራማሪዎቹ በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካኝነት በመራባት የተሰራጩ እንደ ‘አሜሪካን ቡል ፍሮግ’ ያሉ ወራሪ ዝርያዎችን ስርጭት ለመከታተል ዱዪን የተባለውን የቲክ ቶክ መተግበሪያ እየተጠቀሙ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
 
ሳይንቲስቶቹ በማኅበራዊ ሚዲያው መድረክ ላይ የሚለጠፉትን ጽሑፎችን፣ ምስሎች እና ቪዲዮዎችን በመጠቀም በመላው ቻይና ያሉ ሥነ ምህዳራዊ ስጋቶችን ለመፍታት እና ለመቋቋም እየተጠቀሙ እንደሆነ ነው ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት የዘገበው።
 
ከቻይና ሳይንስ አካዳሚ (CAS) የሥነ-እንስሳት ተቋም በተውጣጡት ፕሮፌሰር ሊዩ ዡዋን እና ቡድናቸው "iEcology" የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ዘዴ ከኢንተርኔት የተወሰዱ መረጃዎችን ሥነ-ምህዳራዊ ሂደቶችን ለማጥናት አቀናጅተው እንደሚጠቀሙ ነው ዘገባው የሚያመለክተው።
 
ሳይንቲስቶቹ ከቲክ ቶክ (ዱዪን) የተገኙ ዳታዎችን ከሌሎች ምንጮች ጋር በማገናዘብ አብዛኛውን ጊዜ በሰው ሠራሽ መንገድ የሚሰራጩ በዓይን የሚታዩ እና የማይታዩ ወራሪ ዝርያዎችን እንደሚለዩበት መረጃው ያመለክታል፡፡
 
አንዳንድ ቻይናውያን ከሚከተሉት ቡድሂዝም እምነት ጋር በተያያዘ አዳዲስ ነፍሳትን ሲያገኙ ወደ አካባቢ መልቀቅን እንደ ጥሩ ዕድል እንደሚመለከቱ ተጠቅሶ፣ ይህ ግን ወደ ሥነ-ህይወታዊ ወረራ እንደሚያመራ እና ቀድሞ በአካባቢው ያለውን ሥነ-ህይወት በመጉዳት ሥነ-ምህዳርን ሊያዛባ እንደሚችል ሳይንቲስቶቹ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
 
እንደዚህ ሥነ-ምህዳርን የሚጎዱ ወራሪ ነፍሳትን በቀላሉ ለመለየት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ሰዎች አዳዲስ ነፍሳትን ወደ አካባቢ ሲለቁ ፎቶ በማንሳት እና ቪዲዮ በመቅረጽ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የመልቀቅ ልማድ ስላላቸው ሳይንቲስቶቹ ይህን መረጃ በመሰብሰብ ችግሮቹን ለመለየት እየተጠቀሙበት እንዳሉ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
 
ሊዩ እና ቡድናቸው በምርምራቸው ላይ ትኩረት ያደረጉባቸው በተለይ ‘በአሜሪካ ቡልፍሮግ’ እና ‘ቀይ ጆሮ ባላቸው ዔሊዎች’ ላይ እንደሆነም በዘገባው ተጠቅሷል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top