ኢትዮጵያና ዩጋንዳ በወታደራዊው መስክ በጋራ መሥራት በሚያሥችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተፈራረሙ

1 Mon Ago
ኢትዮጵያና ዩጋንዳ በወታደራዊው መስክ በጋራ መሥራት በሚያሥችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተፈራረሙ
ኢትዮጵያና ዩጋንዳ በወታደራዊው መስክ በጋራ መሥራት በሚያሥችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።
 
የዩጋንዳ መከላከያ ሚንስቴር ሚኒስትር ቪሴንት ባሙላንጋኪ ሴምፒጅ እና የሀገሪቱ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ዊልሰን ዕምባሱ ዕምባዲ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል።
 
ከፍተኛ አመራሮች በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ሲደርሱ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብረሀም በላይ፣ የጦር ሀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ እና ሌሎች ጄኔራል መኮንኖች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
 
የሁለቱ ሀገራት መከላከያ ሚኒስትሮች የሁለትዮሽ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ሲሆን የየሀገራቱ ኢታማዦር ሹሞችም የመግባቢያ ሰነዱን ለማስፈፀም በሚያስችል ዝርዝር ዕቅድ በያዘ ሰነድ ላይ ተፈራርመዋል።
 
የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብረሀም በላይ ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው ገልፀው፤በመረጃ ልውውጥ፣ በወታደራዊ አቅም ግንባታ፣ በሰላም ማስከበር፣ በቀጠናዊ እና ታያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መፈራረማቸውን ተናግረዋል።
 
የዩጋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ቪሴንት ባሙላንጋኪ ሴምፒጅ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበው፤ ለስምምነቱ ተግባራዊነት ዩጋንዳ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
 
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በበኩላቸው ዩጋንዳ ወዳጅ ሀገር መሆኗን እና በፓን አፍሪካኒዝም ረገድ ጭምር በጋር እንደምትሰራ ገልፀው ከዩጋንዳው ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ዊልሰን ዕምባሱ ዕምባዲ ጋር የተደረሱ ዝርዝር ወታደራዊ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
 
የመከላከያ ውጭ ጉዳይ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ተቋሙ ከዚህ በፊትም ከጣሊያን መከላከያ ጋር በጋራ ለመስራት መስማማቱን ጠቁመው፣ይህም ሰራዊቱ ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱን እንደሚያሳይ መግለጻቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገነው መረጃ ያመላክታል።
 
ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ በአፉሪካ ቀንድ ከሰላምና ደህንነት አንፃር የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ የመግባቢያ ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት በቀጠናዊ የደህንነት ተግዳሮቶች ዙሪያ በጋራ መስራት የሚችሉባቸውን ጉዳዮችንም ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top