ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክሩን ማካሄድ የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያፋጠነ ነው፡- ዶክተር ዮናስ አዳዬ

1 Mon Ago
ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክሩን ማካሄድ የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያፋጠነ ነው፡- ዶክተር ዮናስ አዳዬ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ ምክክሩን ማካሄድ የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያፋጠነ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በወላይታ እና በጌዴኦ ዞኖች በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮችን ለመለየት ያዘጋጀው መድረክ በወላይታ ሶዶ እና በዲላ ከተሞች እየተካሄደ ይገኛል።

በወላይታ ሶዶ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ እያከናወናቸው ያለው የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በማፋጠን ላይ ነው።

ኮሚሽኑ እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴም በሰባት ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተሳካ የማህበረሰብ ተወካዮች መረጣ ማከናወኑን በማሳያነት ገልጸዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች የማህበረሰብ ተወካዮች ልየታ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ዴሞክራሲያዊ ስርዓተ ግንባታ እንዲጎለብት ከማስቻል ባለፈ በሀገሪቱ የውይይት ባህልን ለማዳበር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተሳታፊዎች መምረጥ የሚያስችል ግልጽ እና ገለልተኛ አሰራር በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በተወካዮቻቸው በኩል በሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎች ይወክሉናል ላሏቸው አካላት የተለያዩ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በመስጠት ሀሳብና ጥያቄያቸው እንዲደመጥ የሚደረግበት ሂደት መሆኑንም ገልጸዋል።

ለምክክሩ ውጤታማነት በፌዴራል፣ በክልሎች እንዲሁም በከተማ መስተዳደሮች በሚደረጉ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራዎች ላይ ጉልህ ድርሻ የሚኖራቸው አካላት መካተታቸውንና ተገቢውን ተሳትፎ ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ ኮሚሽኑ በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ኮሚሽኑ በጌዴኦ ዞን የማህበረሰብ ተወካዮችን ለመምረጥ ያዘጋጀው መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቁ ጌጡ በወቅቱ እንዳሉት መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልዩነት እና አለመግባባቶች ይስተዋላሉ።

ኮሚሽኑ በቀጣይ ህዝባዊ ውይይቶችን በማዘጋጀት የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የውይይት መድረኮቹ በውክልና እንደሚካሄዱ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ተወካዮችን የመምረጥ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳዎቻቸውን የሚያቀርቡላቸው ተወካዮችን በአግባቡ መምረጥ እንዳለባቸውም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በጌዴኦ እና በወላይታ ዞን የሚካሄደው የማህበረሰብ ተወካዮች መረጣ ለቀጣዮቹ አራት ቀናት እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል።

የተወካዮች መረጣ አካታችነት፣ ግልፀኝነት፣ አሳታፊነትና ተአማኒነትን ባገናዘበ መልኩ እንደሚካሄድም ታውቋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top