በ45 ሚሊዮን ዶላር በተመረጡ አስር ከተሞች የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ማሻሻያ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የኢትጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
በዲስትሪቢዩሽን መስመሮች እርጅና ምክንያት በከተሞች አካባቢ እያጋጠመ ያለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት መልሶ ግንባታና አቅም ማሻሻያ ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱን ነው አገልግሎቱ የገለጸው።
የዲስትሪቢዩሽን መስመር መልሶ ግንባታ እና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው በነቀምቴ፣ በአምቦ፣ በሱሉልታ፣ በቢሾፍቱ፣ በአሰላ፣ በደብረ ብርሃን፣ በዲላ፣ በሆሳዕና፣ በአሶሳ እና በጅግጅጋ ከተሞች መሆኑም ተጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ በሦስት ሎት ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን በአጠቃላይ 195 አዳዲስ ትራንሰፎረመሮችን መገንባት፣ የ1009 ትራንሰፎረመሮች ማሻሸያ እና አቅም ማሳደግ ሥራ እና 1 ሺህ 107 ኪ.ሜ የሚሆን የመካከለኛ ቮልቴጅ መስመር ማስፋፊያና ማሻሻያ ሥራን የሚያካትት ነው።
የፕሮጀክቱ የገንዘብ ምንጭ የዓለም ባንክ ሲሆን ሥራውን ሠርቶ ለማጠናቀቅ 45 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቦለታል።
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ አማካሪ ቅጥር ያጠናቀቀ ሲሆን የፕሮጀክቱን የግንባታ ሥራ የሚያከናውኑ ዓለም አቀፍ ተቋራጮችን የመለየት ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በከተሞች እና በአካባቢያቸው ያለውን የዲስትረቡሽን መስመር አቅም ውስንነት በማሻሻል በከተሞቹ የሚኖረውን የ`ይል መቆራረጥ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ በመቅረፍ የኃይል አቅርቦቱንም ጥራት ያለው እና አስተማማኝ እንዲሆን እንደሚያደርገው ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከዚህ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ ቴክኒካል የኃይል ብክነትን ለመቀነስ፣ አዲስ ኃይል ፈላጊ ደንበኞች ለማገናኘት እና የኃይል አቅርቦቱን ጥራት ያለውና አስተማማኝ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑም ተጠቅሷል።