13ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ እየተካሄደ ነው

1 Mon Ago
13ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ እየተካሄደ ነው
13ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባኤ ''በንግድ ለሕዝብ መድረስ'' በሚል መሪ ቃል ዛሬ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መዲና አቡ ዳቢ መካሄድ ጀምሯል።
 
በድርጅቱ የታዛቢነት መቀመጫ ያላት ኢትዮጵያም በጉባኤው ላይ እየተሳተፈች ነው።
 
በጉባኤው የዓለም የንግድ ድርጅት የ164 አባል አገራት የንግድ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ ናቸው።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትርና የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ተደራዳሪ ገብረመስቀል ጫላ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡመር ሁሴን ኢትዮጵያን ወክለው በጉባኤው ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
 
ጉባኤው የባለብዙ ወገን የንግድ ስርዓት፣ የዓለም የንግድ ድርጅት ተቋማዊ ማሻሻያ እንዲሁም የቀረጥና የታክስ ስርዓት ማሻሻያዎችና የምግብ ዋስትናን ጨምሮ ሌሎች ዓለምን እየፈተኑ ባሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።
 
ንግድና ዘላቂ ልማት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት፣ ግብርናና የአሳ ሀብት ልማት የድጎማ ማዕቀፍ ውይይት የሚደርግባቸው ሌሎች አጀንዳዎች ናቸው።
 
በተጀመረው ጉባኤ የኮሞሮስ እና ቲሞር የአባልነት ጥያቄ መጽደቁንከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራች ነው።
 
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በድርድር አባል ለመሆን በታዛቢነት መሳተፍ የጀመረችው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 ነው።
13ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባኤ እስከ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top