በደም የተከፈለ ዋጋ ሲራከስ

1 Mon Ago
በደም የተከፈለ ዋጋ ሲራከስ

ኢትዮጵያ በታሪኳ ጦርነት ተለይቷት አያውቅም። ጦርነት የታሪኳ አካል ሆኖ የኖረው ግን ሊገፏት የመጡትን ለመከላከል እንጂ የማንንም ድንበር ገፍታ በእብሪት ወረራ በማካሄድ አልነበረም።

የራሷ ነጻነት ብቻ የተሟላ ሰላም እንደማያመጣ ስለምታውቅም የዓለም ሰላም እንዲረጋገጥ የደም ዋጋ ከፍላ ጭምር የራሷን ድርሻ ስትወጣ ኖራለች። በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን እና በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ልጆቿን የገበረችባቸው መስዋዕትነቶች ለዚህ ህያው ምስክሮቿ ናቸው።

በልጆቿ መስዋዕትነት የራሷን ነጻነት ጠብቃ ስለኖረች ስለሌሎች ጭቆና አያገባኝም ብላ የተቀመጠችበት ጊዜም አልነበረም፤ ለዚህም ነው አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ ዋጋ የከፈለችው። በዚህም ደግሞ በቃኝ ብላ አልተቀመጠችም፤ አፍሪካን አሰባበስባ በሕብረት የጉልበተኛውን ዓለም ጫና ለመከላከል ትግል ከጀመረች እነሆ ስድስት አሥርት ዓመታት አልፈዋል።

የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት እንዲመሰረት ኢትዮጵያ ያለፈችውን ውጣ ውረድ ታሪክ ይመሰክራል። ሕብረቱ አሁን ያለው ሕልውና እንዲኖረው አባቶቻችን እንቅልፍ አጥተው ሰርተዋል።

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ዋጋ የከፈለችላቸው አፍሪካውያን ጭምር ኢትዮጵያን ሲገፏት ይታያል። የአፍሪካ ሕብረት ገና ከጥንስሱ ሲጀመር የነበረውን ውጫዊ እና ውስጣዊ ጫና ለመቋቋም ኢትዮጵያ የከፈለችውን ዋጋ የዘነጉ ወገኖች ዛሬ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ከኢትዮጵያ እንዲነሳ ያላቸውን ምኞት ሲገልጹ መስማት ያሳዝናል።

 

የኢትዮጵያን የደም ውለታ የረሳችው ሶማሊያ

ሶማሊያ ለኢትዮጵያ ከጎረቤትም በላይ ነች። የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች በደም፣ በሃይማኖት፣ በባህል እና በቋንቋ የተሳሰሩ የአንድ እናት ልጆች ናቸው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የሶማሊያ ሰላም እና አንድነት የሚገድዳት። ይሁንና ኢትዮጵያ ይህን ብታስብም ሶማሊያን ያስተዳደሩ መሪዎች ግን ሀሳባቸው በተቃራኒ መሆኑን ታሪክ በመዘገባቸው ክስተቶች አረጋግጠዋል።

"ታላቋ ሶማሊያ"ን የመመስረት ቅዠት ይዞ የተነሳው የሶማሊያ መሪ ዚያድ ባሬ በ1968/69 ኢትዮጵያን በመውረር የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ውድ ዋጋ አስከፍሎ በሽንፈት ታሪኩን ደምድሟል። ሶማሊያ ከዚያ በኋላ በጎሳ ተቧድና ሀገር መሆን አቅቷት ሕዝቧ በየአቅጣቸው ተበተነ። ይባስ ብሎም አልሸባብ የተባለው አሸባሪ ቡድን መፈልፈያ ሆነች። አልሸባብ በአካባቢው ሀገራት በተለይም ኢትዮጵያ ላይ የጅሃድ ጦርነት አወጀ።

የሶማሊያ ወንድሞቿ ስቃይ የሚያሳስባት ኢትዮጵያ ግን እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም። አልሸባብን ለመከላከል ድንበሯን አጠናክራ መጠበቅ ብቻ በቂ ቢሆንም፤ የጎረቤት ሰላም ሰለሟ መሆኑን ስለምታውቅ ነው ሠራዊቷን አሰማርታ የተበታተነችው ሶማሊያ መንግሥት እንዲኖራት ያደረገቸው። ይህን ተግባር ላለፉት 17 ዓመታት ቀጥላ አሁንም ልጆቿን እየገበረች ለሶማሊያ ሰላም ውድ ዋጋ እየከፈለች ትገኛለች።

ይህ ብቻም አይደለም፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሶማሊያ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር ስትጋጭ ለማስማማት ብዙ መንገድ ሄዳለች። ለዚህም ሶማሊያ ከኬኒያ ጋር የገባችበትን የድንበር ግጭት ለመፍታት ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት መሪዎች አገናኝታ አስማምታለች።

ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ተለያይተው የኖሩት ሶማሊያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት እንዲኖራቸውም ብዙ ሙከራዎችን አድርጋለች። ኢትዮጵያ አሁንም ይህን የምታደርገው ከጎረቤትም በላይ በደም ትስስር የምትዛመዳት የሶማሊያ ሰላም ሰላሟ ስለሆነ ነው። ሶማሊያ ችግር ውስጥ ስትሆን ዜጎቿ እንደ ስደተኛ ሳይሆን እንደ ቤታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖሩ የፈቀደችውም ለዚህ ነው።

‘ወርቅ ላበደረ ጠጠር’ እንደሚባለው ግን የኢትዮጵያ የደም ዋጋ ተረስቶ ዛሬም የሶማሊያ መንግሥት ከሌሎች የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ሲከስ ይታያል። የቀጣናችንን ችግሮች በጋራ ውይይት እንፍታ የምትለውን ኢትዮጵያን ተራምደው ካይሮ እየሄዱ ኢትዮጵያ ላይ ይዝታሉ። ራሳቸው መቆጣጠር ያልቻሉትን አልሸባብ "ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት በመፈራረሟ አልሸባብ በቀጣናው ላይ ስጋት እየፈጠረ ነው" ብለው ሌላ ኃይል ወደ አካባቢው ለመሳብ ያሴራሉ።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ቤታችንም መጥተው ኢትዮጵያን ለመክሰስ አላመነቱም። ኢትዮጵያ በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ባህሏ መሰረት ተቀብላ ባስተናገደቻቸው "ኢትዮጵያ ካረፍኩበት ሆቴል እንዳልወጣ እና ወደ አፍሪካ ሕብረት ጉባኤ እንዳልሄድ ከልክላኛለች" ብለው ከሰሱ። ለኢትዮጵያን በጎ የማይመኙ አካላትም ክሳቸውን ተቀባብለው አስተጋቡት።

 

ለምን ኢትዮጵያን መክሰስ ፈለጉ?

ትውልደ ሶማሊያዊቷ የሚኒሶታ ምክር ቤት አባል ኢልሃን ኡመር በሚኒሶታ የሚገኙ የሶማሊያ ተወላጆችን ሰብስበው የተናገሩት ንግግር ለዚህ ጥያቄ ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል። እኚህ የምክር ቤት አባል የዚያድ ባሬ ኮሎኔል ከነበሩት አባታቸው ጋር ነው በልጅነት ወደ አሜሪካ የተሰደዱት። ያልተሳካውን የ"ታላቋ ሶማሊያ" ቅዠት ከአባታቸው የወረሱ የሚመስሉት ኢልሃን ኡመር "መሬታችንን እናስመልሳለን፤ ኢትዮጵያም ኬንያም የወሰዱትን መሬት ይመልሷታል፤ እኔ እዚህ ምክር ቤት ውስጥ እስካለሁ ድረስ ጥቅማችንን እናስጠብቃለን …" በማለት ከሶማሊያ ምክር ቤት አባል እንጂ ከአንድ የአሜሪካ ግዛት ምክር ቤት አባል የማይጠበቅ አስተያየት ሰንዝረው ነበር። በዚህ ድርጊታቸውም ከአሜሪካ ሴኔት አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር የምናስታውሰው ነው።

የኚህ የምክር ቤት አባል ንግግር ዝም ተብሎ እንደ ተራ ጉዳይ የሚታለፍ ሳይሆን ከጀርባው ያለውን ሴራ የምናይበት ነው። የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ መሐመድ በዚያው ሰሞን ወደ ግብፅ ሄደው ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ መወያየታቸው፣ የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ "ሶማሊያን የነካ ማንንም ቢሆን ግብፅ አትታገስም" ማለታቸው፣ የዓረብ ሊግ መግለጫ ሲቀጣጠሉ ሶማሊያ የሌሎችን አጀንዳ ተጭና የምትጋለብ ፈረስ መሆኗን መረዳት ይቻላል።

የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ሲፈርሱ እና ሕዝባቸው ሲሰደድ፣ ፍልስጥዔማውያን ምድር ሲዖል ስትሆንባቸው ትንፍሽ ያላለው እና ምንም የማይፈይደው የዓረብ ሊግ ኢትዮጵያ ላይ መግለጫ ሲያወጣ ስናይ ሶማሊያ የሌሎች አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንደሆነች ሌላው ማሳያ ነው።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን በከሰሱበት መግለጫቸው "ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ መሆን አትችልም" ለማለት የሄዱበት ርቀት የተደበቀውን አጀንዳ የሚያሳብቅ ነው። ድብቅ አጃንዳ ባይኖርማ መጀመሪያውንም ራሳቸው ችግር ፈጣሪ በነበሩበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ባልከሰሱ፣ ከተነሱበት የሶማሊላንድ ጉዳይ ጋር የማይገነኝ አጀንዳም ባላነሱ ነበር። በተመሳሳይ ጊዜ ይህን አጀንዳ ተቀባብለው የሚያራግቡ ባዳዎችን እና ባንዳዎችን ስንመለከት ደግሞ ነገሮች ግልጽ እየሆኑልን ይሄዳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ከኢትዮጵያ ሲወስድ ምንም የማይለው ዓለም ኢትዮጵያ የሚገባትን ድርሻ ስትጠይቅ ግን ኢትዮጵያ ላይ መዝመቱ እንቆቅልሽ ነው። የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ በታሪኳ በተግባር እንደኖረችው፣ ወደፊትም ለጎረቤቶቿ የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት ከሁሉም ጋር በሰላም እና በመግባባት የመኖር ዲፕሎማሲ መከተሏን ትቀጥላለች።

ለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top