የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት 3ኛ የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤዉን በዛሬው ዕለት ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ምክር ቤቱ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚኖረው ቆይታ የክልሉን የ2016 የግማሽ ዓመት የ6 ወራት የልማትና መልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ጨምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የስራ ክንውን ሪፖርቶችን አድምጦ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የቀጣይ ግማሽ ዓመት የተከለሰ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ እንዲሁም የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን በመገምገም ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ተገልጿል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ ባንቺአየሁ ዲንገታ፤ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግግር ምክር ቤቱ የተጣለበትን ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አባላት በህገ መንግስቱ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የህዝቡ ጥያቄ መልስ ስለማግኘቱ እና መልካም አስተዳደር ስለመስፈኑ እንዲሁም የወከላቸው ህዝብ የልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን በንቃት ተከታትለው ማስፈፀም እንደሚኖርባቸውም ዋና አፈጉባኤዋ አሳስበዋል።
በሚፍታህ አብዱልቃድር