በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ በጂግጂጋ ከተማ የተገነባው የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ ተመረቀ

5 Mons Ago
በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ በጂግጂጋ ከተማ የተገነባው የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ ተመረቀ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካውን መርቀው ከፍተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፥ የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ ግንባታዎችን ጀምሮ በማጠናቀቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

በሶማሌ ክልል ያለውን ሰፊ የመልማት አቅም በመጠቀም በስንዴ ምርት እና ምርታማነት ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የስንዴ ምርትን ለዳቦ ቤት ግብዓትነት በማዋል፣  ከዳቦ ቤቶች የሚገኝ ተረፈ ምርትን ደግሞ ለእንሰሳት መኖ በማዋል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በተጨማሪም በዕለቱ በሶማሌ ክልል ያስጀመሩት እና በ‘ገበታ ለትውልድ’ መርሀ ግብር የሚገነባው የሸበሌይ ሪዞርት የሶማሌ ማህበረሰብን ባህል እና አኗኗር በሚያንፀባረቅ መልኩ የሚገነባ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የጂግጂጋ ከተማን ማዕከል በማድረግ በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ የሶማሌ ተወላጆችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩት እነዚህ ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ ሁሉም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፥ በጽ/ቤታቸው የተገነባው የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ ህብረተሰቡን በተጨባጭ ተጠቃሚ እንዲያደርግ እና የታቀደለትን ግብ እንዲያሳካ ሁሉም በባለቤትነት ስሜት ሊጠብቀውና ሊያስተዳድረው ይገባል ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው፥ የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ከዚህ ቀደም በጂግጂጋ ከተማ 2 ትምህርት ቤቶችን ገንበቶ ለህብረተሰቡ ማስረከቡን አስታውሰው፤ ጽ/ቤቱ በዕለቱ የተመረቀውን የዳቦ እና ዱቄት ፋብሪካ በተጨማሪ ገንብቶ ወደ ስራ በማስገባቱ ምስጋና አቅርበዋል።

ከሚድሮክ ኢንቬስትመንት ግሩፕ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተገነባው ፋብሪካው በቀን 300 ሺህ ዳቦ እና 420 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፤ ጽ/ቤቱ አስገንብቶ ወደ ስራ ያስገባው 8ኛው ፋብሪካ መሆኑም በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

በቴዎድሮስ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top