የሳተላይት መረጃዎችን ለሀገራትና ድርጅቶች መሸጥ የሚያስችል አገልግሎት ተጀመረ

10 Mons Ago 900
የሳተላይት መረጃዎችን ለሀገራትና ድርጅቶች መሸጥ የሚያስችል አገልግሎት ተጀመረ

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሕዋ ንግድ የሳተላይት መረጃዎችን ለሀገራትና ድርጅቶች መሸጥ የሚያስችላትን አገልግሎት ዛሬ በይፋ አስጀምራለች።

የመረጃ ሽያጩ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገኝ እንደሆነም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ የሳተላይት መረጃውን የምትሸጥበት አገልግሎት የሚሰጠው በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ያስገነባው የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን አለማየሁ፣ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች አገልግሎቱን በይፋ አስጀምረዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ያስገነባው የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም መመረቁ የሚታወስ ነው።

ሶስት ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የተደረገበትና 7 ነጥብ 3 ሜትር ከፍታ ያለው ጣቢያ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ፈጅቷል።

ጣቢያው የሳተላይት መረጃዎችን የማከማቸት፣ የመተንተንና ወደ ምስል የመለወጥ ስራ የሚከውን ሲሆን ከመሬት ምልከታ ሳተላይቶች እስከ 0 ነጥብ 5 ሜትር የምስል ጥራት ያለው የሳተላይት መረጃ መቀበል የሚችል ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን አለማየሁ ኢንስቲትዩቱ በሳይንስ ዘርፉ ተጨባጭ እድገት እንዲመጣ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢንስቲትዩቱ ጣቢያውን በመጠቀም የሳተላይት መረጃ አገልግሎት ለአገራትና ለድርጅቶች በመስጠት ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበትን ሁኔታ መፍጠሩ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top