የዚህ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማሳያ - "ፀሐይ"

5 Mons Ago
የዚህ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማሳያ -  "ፀሐይ"

የጥንት ኢትዮጵያ ሥልጣኔ አስደናቂ ነው ሲባል በዓለም ላይ ከነበሩት ኃያላን ሀገራት አንዷ የሆነችበት ነው:: በዚያን ጊዜ ግዛቷ ሰፊ፤ ዓለም አቀፍ ንግዷም የተሳለጠ ነበር፡፡ ምስክሮቿም ሺህ ዘመናትን ተሻግረው ለኛ ዘመን የደረሱ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፉ እንደ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ጀጎል እንዲሁም የድንጋይ ላይ እና የብራና ጽሑፎቿ ናቸው፡፡

ታዲያ ይህ ዓለምን ያስደነቀ እና እኛንም የሚገርመን ስልጣኔ አክትሞ እንዴት ዛሬ ያለንበት ደረስን የሚለው እንቆቅልሽ ነው:: ከነዚህ ስልጣኔዎች ቀጥሎ የነበሩ ሙከራዎች ደግሞ በውጫዊ ጫናዎች እና በውስጣዊ ሽኩቻዎች ምክንያት አንድ ዘመን ላይ የተጀመረው ሥልጣኔ ወደ ሌላው ዘመን እንዳይሸጋገር ሲያደረግ ቆይቷል:: ይህም ብቻ አይደለም የእኛ የነበረው ታሪካችንን የሰነዱ ቅርሶቻችን የሌሎች እስኪመስሉ ድረስ በታቀደ መልኩ የሥልጣኔ ምልክቶቻችን ተሰርቀው ሲወሰዱ ኖረዋል፡፡ በውጭው ዓለም ከለንደን እስከ ዋሽንግተን ሙዚየሞች እና የታሪክ እና መዛግብት ክምችት ክፍሎች ያሉ ከብራና ጽሁፍ እስከ ቁሳዊ ቅርስ መገኛ መሆናቸው ማሳያ ናቸው::

በዚህ ክፍለ ዘመንም ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል የተደረጉ ሙከራዎች በተመሳሳይ ጫናዎች ሳይቀጥሉ ቀርተዋል፡፡ በአቪየሺን ኢንዱስትሪ ታሪክ አሁን በዓለም አሉ ከተባሉት የዓለማችን አውሮፕላን አምራቾች ተርታ ሊያሰልፈን የነበረው ሙከራ ተሰርቆ ከሽፏል፡፡ እኛም ቆም ብለን አባቶቻችን የጀመሯቸውን አስደናቂ ሥራዎች ከመመርመር ይልቅ እርስ በርሳችን ስንሻኮት ከምንም ሳንሆን እዚህ ደርሰናል፡፡ አሁን ግን የተስፋችን ፀሐይ የምትመለስበት ዘመን ላይ የደረስን ይመስላል፡፡

ከ88 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተሰራችው "ፀሐይ" አውሮፕላን በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ ሀገሯ ተመልሳለች፡፡ ይህም ስብራታችንን ጠግኖ ተስፋችንን የሚመልስ ይሆናል የሚል እምነት እንዲኖር አስችሏል፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ቅርሶች ለምን ተዘረፉ? ለምንስ ሳይመለሱ ለብዙ ዘመናት ቆዩ? አሁን መመለሳቸው አንድምታው ምንድን ነው?

በቅርሶች አማካኝነት የተዘረፈው አፍሪካዊ ማንነት

አውሮፓውያን አፍሪካን ቅኝ ሲገዙ የተቀራመቱት የተፈጥሮ ሀብቷን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንስ የአፍሪካን ማንነት፣ ሥልጣኔ እና ታሪክ የሚያሳዩ ነገሮችን ሁሉ ነው የወሰዱት፤ የቀሩትንም አውድመው የአፍሪካን ማንነት በራሳቸው ማንነት ለመተካት ሰርተዋል፡፡ ለዚህም በአውሮፓ፣ አሜሪካ እና ሌሎች የዓለም ክፍሎች ቤተ መዘክሮች ውስጥ ያሉ የአፍሪካ ቅርሶች ምስክሮች ናቸው፡፡

የአፍሪካውያንን ቅርስ ሲዘርፉ የሚዘርፉት ቁስን ብቻ ሳይሆን ማንነትን፣ ሥነ-ልቦናን እና ባህልን ነው፡፡ ብዙ አፍሪካውያን ከራሳቸው ማንነትም ሳይታረቁ፣ ከምዕራባውያኑ ባህል እና ማነት ሳይዋሀዱ የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተው የቀሩትም ለዚህ ይመስላል፡፡

አፍሪካ የራሷ ባህል፣ ሥልጣኔ፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ እሴት እና ታሪክ የነበራት እና አብዛኛውን በቃል እና በምልክቶች ቀምራ ለትውልድ ስታስተላልፍ የነበረች አህጉር ነች፡፡

ታዲያ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የራሷን ማንነት እና የደለበ ሀብት የነበራትን አፍሪካን ሊቀራመቱ ሲያስቡ "ጨለማው አህጉር" ብለው የዳቦ ስም በመስጠት "ጨለማውን አህጉር ልናሰለጥን መጣን" ብለው ወረሯት፡፡ ከወራረው በፊት ማንነትን የማስጣል ትልቅ የሥነ-ልቦና ሥራ ሠርተው አፍሪካን ራሷን እንድትጥል አድርገው አዘጋጅተው ነው፡፡

ለዚህም ነው በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረፉ የአፍሪቃ ቅርሶች መመለስ እንዳላበቸው ክርክር የሚነሳው። እነዚያ የተወሰዱ ቅርሶች በትውልድ መካከል ያለውን ቅብብሎሽ የሚያጠናክሩ እና ለፈጠራ መነሻ የሚሆኑ ናቸው፡፡

ነገር ግን ምዕራባውያኑ ከአፍሪካ የወሰዷቸውን ቅርሶች ለመመለስ ፈቃደኛ የማይሆኑትን ያክል አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መሪዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸው ተነሳሽነት ለውስጥ ፖለቲካዊ ሽኩቻ የሚሰጡን ያክል ትኩረት የለውም፡፡ ይሁን እንጂ ምዕራባውያኑ በራሳቸው በጎ አሳቢ ምሁራን ጭምር ግፊት ስለበዛባቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ቅርሶቹን የመመለሱ በጎ አዝማሚያዎች እና ጅምሮች እየታዩ ይገኛሉ፡፡

ፈረንሳይ እና እንግሊዝ በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ ሀገራትን ቅርሶች መመለስ ጀምረዋል፡፡ ናይጄሪያ እና ቤኒን ደግሞ ለዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ቅርሶቹ ቢመለሱ ምን ጠቀሜታ አላቸው?

አብዛኛዎቹ ከአፍሪካ የተወሰዱ ቅርሶች የአፍሪካ ትክክለኛ ማንነት እና ምዕራባውያን እንደሚሉት አፍሪካ ‘ጨለማ አህጉር’ እንዳልሆነች እና የራሷ ሥልጣኔ እና ቀለም እንዳላት የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ቅርሶች ሲመለሱ ትውልዱ አያቶቹ እና ቅድመ አያቶቹ የት እንደነበሩ የሚረዳበት እና በመሃል የተፈጠሩ ክፍተቶች የሚያውቅበት ነው፡፡ እንደዚህ ሲሆን ደግሞ ራሱን የሚሆን ትውልድ ይፈጠራል፡፡ ይህም የአፍሪካ ትንሳኤ ምልክት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡

በዓለም ላይ የተበተኑ የኢትዮጵያ ቅርሶች

ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የምትለየው በአውሮፓውያን ቅኝ አለመገዛቷ ነው፡፡ ነገር ግን በሌሎች አፍሪካውያን ላይ የደረሰው የቅርሶች ዘረፋ አልቀረላትም፡፡ ቅርሶቻችን የተዘረፉት በጉብኝት ስም፣ በወረራ፣ ድቃቂ ሳንቲም በሚፈልጉ የሀገራችን ልጆች አማካኝነት ወደ ውጭ በመሸጣቸው ነው፡፡

በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአባይን ምንጭ ፍለጋ በሚል ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ጀምስ ብሩስ መጽሐፈ ሄኖክን ጨምሮ የተለያዩ የብራና መጻሕፍትን ይዞ ነው ወደ ሀገሩ የተመለሰው፡፡

ከዚህ የመካከለኛው ዘመን ቀጥሎ የኢትዮጵያ ቅርሶች የተዘረፉት የመቅደላ ጦርነት ጊዜ ነው፡፡ እንግሊዞች ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ግጭት ውስጥ በገቡበት ወቅት የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ የነበሩ ወገኖቻችን መግቢያ መውጫው የታጠረባቸው መይሳው ካሳ ትላልቅ ቅርሶችን ይዘው መቅደላ ላይ የመጨረሻውን ቀን መጠበቅ ጀመሩ፤ ይህም ጦርነት አባ ታጠቅ ራሳቸውን እንዲያጠፉ ምክንያት ሆነ፡፡ እንግሊዞችም ወደ መቅደላ አምባ ገብተው በርካታ የብራና መጻሕፍትን፣ የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳትን እና ሌሎች ያገኟቸውን ንብረቶች በወቅቱ በነበሩት ማጏጏዣ እንስሳት ሁሉ ጭነው እንደ ወሰዱ የራሳቸው ሰዎች የጻፉት ታሪክ ምስክር ነው፡፡

እንግሊዞቹ የአጼ ቴውድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁን እና እናቱን ይዘው ወደ ሀገራቸው ጉዟቸውን ጀመሩ፡፡ የልዑል ዓለማየሁ እናት በመንገድ ላይ ስላረፉ እንግሊዞቹ ህጻኑን ልዑል ይዘው ወደ ሀገራቸው ተጓዙ፡፡ ምስኪኑ ልዑል ዓለማየሁ እዚያው እያደገ እያለ በ18ኛው ዓመቱ አካባቢ ህይወቱ አለፈ፡፡

ሌላኛው የኢትዮጵያ ቅርሶች የተዘረፉበት ክፉ አጋጣሚ የጣሊያኑ የአምስት ዓመታት ወረራ ነው፡፡ በዚያ አምስት ዓመታት ወረራ ጣሊያን ያላወደመው እና ያልዘረፈው የኢትዮጵያ ቅርስ የለም፡፡ የአክሱም ሀውልት፣ የጥቁር አንበሳ ሀውልት፣ እና በርካታ ንዋያተ ቅድሳት እና ሌሎች ለኢትዮጵያ ይጠቅማሉ ያላቸውን ቅርሶች ሁሉ ሰብስቦ ወስዷቸዋል፡፡ የቀሩትንም አውድሟቸዋል፡፡ ለዚህም ምስክር የፈለገ ሮም ሄዶ በቤተ መዘክሮቹ ያሉ የብራና መጻሕፍትን እና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳትን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡

በቅኝ ግዛት ወረራ ወቅት ምዕራባውያን ሀገራት የዘረፏቸውን ቅርሶች ለማስመለስ ብዙ ጥረት ተደርጎ አክሱም፤ የላሊሊላ አፍሮአይገባ መስቀል፤ የአጼ ቴዎድሮስ ቆንዳላ እና በርካታ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ተመልሰዋል።

የተሰረቀችው የህልማችን፤ ፀሐይ

በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች ራሷን እንድትችል በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል፤ ከነዚህም መካከል የአቪየሽን መጀመር፣ የቴሌኮሙኒኬሽን መስፋፋት እና የአየር ኃይል መቋቋም ዘመን ተሻጋር ሥራዎች ናቸው፡፡

በአቪየሺኑ ከተሞከሩ አስደናቂ የሥልጣኔ አብነቶች መካከል አውሮፕላኖቸን ከውጭ ከማምጣት ባሻገር በሀገር ውስጥ ለማምረት የተደረገው ሙከራ የንጉሡ ሩቅ አሳቢ ራዕይ ነበረ። ጀርመናዊው የንጉሡ አውሮፕላን አብራሪ ሉድዊግ ዌበር ከኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የመጀመሪያውን አውሮፕላን ሠርተዋል። ሦስት አውሮፕላኖችን በሀገር ውስጥ ለመሥራት ታቅዶ ሥራው ቢጀመርም አንዷ ብቻ ተጠናቅቃ የሙከራ በረራ እንዳደረገች ጣሊያን ኢትዮጵያን ወረረች፡፡

ተገጣጥማ የተጠናቀቀችው አውሮፕላን ባለ 115 የፈረስ ጉልበት ሞተር የተገጠመላት ባለ ሰባት ሲሊንደር ነበረች። ክንፎቿ የተሰሩት ከእንጨት ሲሆን የተቀረው የአውሮፕላኗ ክፍል ብረት ሆኖ መስኮቱ በፕላስቲክ የተሸፈነ ነው፡፡ ይቺ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የተገጣጠመችው አውሮፕላን በጃንሆይ ልጅ ልዕልት ፀሐይ ስም ተሰየመች።

ፀሐይ በአየር ላይ መቆየት የቻለችው በጠቅላላው ለሰላሳ ሰዓታት ሲሆን፣ የሞሶሎሊ ፈሺስት ወራሪ ኃይል አዲስ አበባን ሲወር ጀርመናዊው መሐንዲስ ዌበር ወደ ሀገሩ ሲሄድ፣ ፀሐይም ወራሪው እጅ ወደቀች፡፡

ጣሊያኖቹ ልክ እንደ አክሱም ሀውልት ሁሉ ፀሐይንም ጭነው ወደ ጣሊያን ወሰዷት፡፡ ፀሐይ በመጀመሪያ በ ‘Caserta Aeronautical Museum’ ከዚያም ‘Italian Aviation Museum “the airplane of the Negus” መጎብኘት ጀመረች።

በ1940 ዓ.ም በፓሪስ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በተደረሰ የሰላም ስምምነት አንቀጽ 37 መሰረት ማንኛውንም በአምስቱ ዓመታቱ የወረራ ዘመን ከኢትዮጵያ የዘረፈችውን ቅርስና ንብረት በአስራ ስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ልትመልስ ጣሊያን ቃል ገብታ ነበር። ይሁን አንጂ ጣሊያን የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ቅርሶቹን ሳትመልስ ቆይታለች፡፡ በተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት እና የዲፕሎማሲ ሥራ ግን የአክሱም ሀውልት ቀደም ብሎ ተመልሶ የነበረ ሲሆን፣ የተሰረቀችው የኛ ፀሐይም ከተወሰደች ከ88 ዓመታት በኋላ ወደ ቤቷ ፊቷን መለሰች፡፡

በመንግሥትና በሀገር ወዳድ ዜጎች ጥረት ወደ ሀገሯ የተመለሰችው አውሮፕላን ኢትዮጵያ በአቪየሽን ዘርፍ የነበረችበትን ደረጃ ማሳያ ነች፡፡ መንግሥት አሁን እያደረገ ያለው ድጋፍ በሀገር ወዳድ ዜጎች የኢትዮጵያን ውደ ቅርሶች ለማስመለስ ሲያደርጉት ለነበረው ጥረት ከፍተኛ አቅም ይሰጣል፡፡

ይህም እንደ ሀገር ለታሪካችን የሰጠነው ዋጋ ትልቅ እየሆነ መምጣቱን ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካላት ፀሐይን ለማስመለስ ተደርገው የነበሩት ጥረቶች ፍሬ ሳያፈሩ ቆይተው በመንግሥት ደረጃ ሲያዝ መሳካቱ የዚህ የመንግሥት ፍላጎት እና ጥረት ውጤት ነው፡፡ ፀሐይን ለማስመለስ የተደረገው ጥረት ጥበብ የተሞላበት እና ዲፕሎማሲያው ተግባር የታከለበት መሆኑን መግለጫው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቀጥታ በጉዳዩ ላይ መሳተፋቸው ነው፡፡ በንጉሡ ጭምር የተደረጉ ፀሐይን የማስመለስ ተደጋጋሚ ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተው አሁን መሳካቱ ትኩረቱን ብሔራዊ ክብርን ማስጠበቅ በሆነው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ፍሬ እያፈራ መሆኑን ማሳያ ነው።

የፀሐይ መመለስ ምን አንድምታ አለው?

ታሪኳ እንደሚያሳየው ፀሐይ በመጀመሪያ ሙከራዋ ለ30 ሰዓታት አየር ላይ ቆይታለች፡፡ ይህ ስኬት ዛሬ በዓለም ላይ ስመ ጥር የሆኑ እንደ ቦይንግ ያሉ አውሮፕላን አምራቾች ከጀመሩበት መነሻ የተሻለ እንጂ ያነሰ እንዳልነበረ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ የፀሐይ ሙከራ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ከ88 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ በአቪየሽኑ ዘርፍ ምን ደረጃ ላይ ልትሆን እንደምትችል ማስላት ነው፡፡ ይህን የአባቶቻችን ህልም ለዛሬው እና ለቀጣዩ ትውልድ ለማሳየት እና ቁጭት ለመፍጠር እንደ ፀሐይ ያሉ ተጨባጭ ሙከራዎችን ማሳየት ወሳኝ ነው፡፡

አሁን ላይ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ሁሉ ስልጣኔ ከምእራባውያን ብቻ የሚቀዳ ለሚመስለው ሁሉ እንደሱማ አይደለማ ለማለት ፀሐይ ምስክር ትጠራለች:: በአክሱም ዘመን የነበረው እንደፀሐይ ያበራው ስልጣኔ ጠፍቷል ሲባል በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዳግም የስልጣኔ ብርሃን ታይቶ በቅዱስ ላሊበላ ዘመን ብርሃኑ ለሁሉም ተገለጠ:: ይህ ዘመንም ለትውልዱ አዲስ ብርሃን አጎናፅፎ አስገራሚ ስራዎችን እንዲሰሩ አስችሏቸው ለእኛም ተርፏልናል::

ከዚህ ዘመን በሗላ አሁንም ይሄ የስልጣኔ ብርሃን ለመጨረሻ ጊዜ አጥፍተነዋል ለሚሉ እኩያን የደስታ ጊዜ የመጣ መስሎ ተስተውሏል:: በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ደግሞ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ተጠንስሶ በአፄ ምኒልክ የተቋደስነው የስልጣኔ መስመር በቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ዘመን እንዲበራ ያልተሞከረ አልነበረም:: የስልጣኔ ብርሃኑ በጭላንጭል ላይ እያለ እንደገና ተዳፈነ:: እና አሁን ይህን ታሪካችንን ላስተዋለ አክሱም እና ላሊበላን ለመረመረ ፀሐይ ደግሞ ለተመለከተ ትውልድ እውነትም የስልጣኔያችንን ብርሃን ማብራቱ አይቀርም ያስብላል::

ይህም ትውልዱ ወደ ራሱ ተመልሶ የት እንደ ነበርን እና እንደተነሳነው ብንቀጥል የት እንደርስ እንደነበረ እንዲያውቅ ያደርገዋል፡፡ ለፈጠራም መነሻ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ፀሐይ እንደ ስሟ የተስፋ ፍንጣቂያችን ነች የምንለው፡፡ ፀሐይ ቁጭት ነች! ፀሐይ ተስፋ ነች! ፀሐይ ማንነታችን ነች! ፀሐይ የአባቶቻችን ሩቅ አሳቢነት ማሳያ ምስክር ነች! ስለዚህም የፀሐይ መመለስ ቅርስን አስመልሶ ሙዚየም ውስጥ አስቀምጦ ከማስጎብኘት የላቀ ትርጉም አላት፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top