ለ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

2 Mons Ago
ለ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ለ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ በርካታ የዝግጅት ምዕራፎች ሲካሄዱ መቆየቱን ጠቁመዋል። 

በዚህም ከተማዋን የማስዋብና የማፅዳት፣ እንግዶችን የሚቀበሉ ሆቴሎች የመለየትና የማዘጋጀት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እና የፀጥታ አካላት ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል። 

ሕብረተሰቡ በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ለእንግዶች አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። 

''የአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት በነፃ የተገኘ አይደለም ''ያሉት አምባሳደር መለስ፤ በትውልድ ቅብብሎሽ የተሰሩ ሥራዎች ውጤት መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ፀንቶ እንዲኖር የአሁኑ ትውልድ የቤት ሥራ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ አህጉር አቀፍ ጉባዔ የኢትዮጵያን በጎ ገፅታ ለመገንባት ጭምር ሰፊ ሚና የሚጫወት ይሆናል ሲሉ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የዘንድሮው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የፊታችን የካቲት  9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ 44ኛው የአባል ሀገራቱ  የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ከመሪዎች ጉባዔ ቀደም ብሎ የካቲት  6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ሕብረት የ2024 መሪ ቃል "ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ስርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራት እና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት“በሚል ይካሄዳል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top