የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ነገ ይመረቃል

2 Mons Ago
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ነገ ይመረቃል

አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በነገው እለት ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ያስመርቃል።

የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎች እንዳሉት ተጠቅሷል።

በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ በርካታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ቤተ-መጽሀፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየም ያካተተ ነው።

ከተመሠረተ 80 ዓመታትን የተሻገረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ለዚህም በመላው ሀገሪቱ 38 ቅርንጫፎችን በመክፈት በቅርቡ የጀመራቸውን ሶማሊኛ እና አፋርኛን ጨምሮ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች አስተማማኝ የዜና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም የኢትዮጵያን ገፅታና እውነታ ለዓለም ተደራሽ እያደረገ ነው።

ኢዜአ በ2022 በአፍሪካ ተምሳሌት፣ አስተማማኝና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዜና ምንጭ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት በላቀ ብቃት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

የስርጭትና ተደራሽነት አድማሱን በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋት በኬንያና በጅቡቲ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ኢዜአ በ1934 ዓ.ም በወቅቱ የጽሕፈት ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራ በነበረው ተቋም፣ የጋዜጣ እና ማስታወቂያ ጽህፈት ቤት ስር እንደ አንድ የሥራ ክፍል መቋቋሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የሚለውን መጠሪያና የዜና አገልግሎት ደረጃ ያገኘው በ1960 ዓ.ም በወጣው የመጀመሪያው የማቋቋሚያ አዋጅ ነው።

በአዋጅ ቁጥር 1115/2011 በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ዋነኛ የዜና ምንጭ በመሆን ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠርና የሀገሪቱን ገጽታ የመገንባት ተልዕኮ ተሰጥቶታል።

ኢዜአ እስከ አሁን በመጣበት ረጅም የአገልግሎት ዘመን በሀገሪቱ በተመዘገቡ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች ላይ የራሱን አሻራ እያሳረፈ ጉዞውን ቀጥሏል።

አገልግሎቱ በአዲስ የከፍታ ምዕራፍ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ዜና እና ዜና ነክ ዘገባዎችንና ፕሮግራሞችን በፍጥነትና በጥራት ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርግ ይሆናል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top