የማታንቀላፋዋ ከተማ - ሞስኮ

6 Mons Ago
የማታንቀላፋዋ ከተማ - ሞስኮ
የቱሪስቶችን ቀልብ የሚገዙ ፓርኮችን፤ ምቹ እና ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን የገነባች፤ ብዝኃነት መለያዋ የሆነና መቼም የማታንቀላፋዋ ከተማ - ሞስኮ፡፡
 
መገኛዋ በሩሲያ ምዕራባዊ ክፍል ሲሆን፣ እ.አ.አ በ2022 በወጣ መረጃ ከ12 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንደሚኖርባት ተገልጿል፡፡ አጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 2 ሺህ 511 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው፡፡
 
ከተማዋ በሞስክቫ ወንዝ አጠገብ የተመሰረተችው በ12ኛው ከፍለ ዘመን ማለትም በ1147 በንጉሥ ሪዶልጎሩኪ ነበር፡፡ እ.አ.አ እሰከ 1712 የሩሲያ ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች፡፡
 
ይሁን እንጂ እ.አ.አ በ1712 የሩሲያ ዋና ከተማ ሴንት ፒተርስበርግ እንድትሆን ተወሰነ። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ የሞስኮ መኳንንት እና ነጋዴዎች ከሞስኮ ወደ አዲሷ ዋና ከተማ ተዛወሩ። በ1812 ደግሞ ሞስኮ በታሪኳ አስከፊ የእሳት አደጋ ደረሰባት። እነዚህ ክስተቶች ተደማምረው የከተማዋን ዕድገት አዘገዩት። እ.ኤ.አ በ1917 ከተካሄደው የሩሲያ አብዮት በኋላ የሶቭየት ኅብረት ስትመሰረት ሞስኮ እንደገና የኅብረቱ ዋና ከተማ ሆናለች፡፡
 
ሞስኮ በሩሲያ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ በህዝብ ብዛቷ ቀዳሚ ስትሆን የሩሲያ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፣ የኢንዱሰትሪ፣ የሳይንስ እና የትምህርት ማዕከል ናት፡፡
 
ከተማዋ 5 የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ 300 ጣቢያዎች ያሉአቸው 19 የባቡር መስመሮች፣ 257 ዩኒቨርስቲዎች፣ 440 ሙዚየሞች፣ 500 ቤተመፅፍት፣ 121 ፓርኮችና መናፋሻዎች አሏት።
 
ሞስኮ በአብዛኛው ከአትላንቲክ ውቅያኖስ የሚመጣ ናፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚስተዋልባት እና በበረዶ የተሸፈነች ናት። የሩሲያ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ እና የባህል ማዕከልም ናት፡፡ የሞስኮዋ ክሬምሊን የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ነች።
 
ሞስኮ ዘመናዊ የመሰረት ልማት ያሟላች ሲሆን፣ በየዓመቱ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን፣ ፌስቲቫል፣ ኩነቶችን፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን እንዲሁም ስፖርታዊ ውድድሮችን በማስታናገድ ትታወቃለች።
 
ከተለያዩ ሀገራት ተማሪዎችን በነጻ የትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) በመቀበል ከቀዳሚዎቹ የዓለም ከተሞች መካከል ተጠቃሽ ናት።
ከ4ሺ በላይ ጂምናዚየሞች፣ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችሉ የስፖርት መሰረተ ልማት አላት።
በከተማዋ ያሉት ከ120 በላይ ዘመናዊ የመዝናኛ ፓርኮች ሞስኮን በቱሪስቶች ዘንድ ተመራጭ አድርገዋታል።
 
በ367 ቋንቋዎች የተፃፉ ከ45.5 ሚሊዮን በላይ መፅሃፍትንና የህትመት ውጤቶችን የያዘው በአውሮፓ ትልቁ ቤተ መፅሀፍት የሩሲያ ስቴት ላይበራሪ መገኛው የሞስኮ ከተማ ነው።
 
ላይብራሪው ኢንተርኔት በተገጠመላቸው ዘመናዊ ኮምዩተሮች፣ ኤሌክትሮኒክ ዶክመንቶችን መፈለጊያ አማራጮች እና ዘመናዊ ካፍቴሪያ እና ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ለደንበኞች ይሰጣል።
 
በመዲናዋ በሚገኙ ሙዝየሞች ለ24 ሰዓታት የሚዘጋጁ የመዝናኛ ኩነቶች፣ ኮንሰርቶች እና ዓመታዊ የጥበብ ዝግጅቶች የቱሪስችን ቀልብ ከመሳባቸውም በላይ ሞስኮን 'የማታነቀላፋዋ ከተማዋ አሰኝተዋታል።
 
ከተማዋ ዘመናዊ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት፤ ከመሬት ውስጥ የተዘረጋ ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት (ሜትሮ) ሥርዓት አላት።
ሞስኮ ከመገኛዋ ሞስኮቫ ወንዝ ዳርቻ ወደ ከተማ ማእከል ለመገናኘት 49 ድልድዮችን ገንብታለች። ከተማዋ 10 ክፍል ከተሞችና 123 የአከባቢ አስተዳደሮች አሉአት።
 
በላሉ ኢታላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top