የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

7 Mons Ago
የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሒደት ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ ብዙ ተግባራትን ይጠይቃል ብለዋል።

ለዚህም ኮሚሽኑ ተቋሙን በግብአት እና በሰው ሀይል የማደራጀት፣ ወደ ተሀድሶ የሚገቡ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመለየት እና ከክልሎች ጋር በስራዎቹ ላይ መግባባት የሚፈጥሩ መድረኮችን ማካሄዱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ መልሶ ወደ ማቋቋም ተግባር ከመገባቱ በፊት በድጋሚ የማጣራት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ የማድረጉ ስራ ከፍተኛ ሀብት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

መንግሥት ለብሔራዊ ተሃድሶው ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ከፍተኛ ሙዓለ ንዋይ ፈሰስ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀልና መልሶ የማቋቋም ስራ ለሀገሪቱ ልማትና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሚናው ቀላል እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

በተለይም በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ ተዋጊዎች ወደ ሰላም ተመልሰው የኢኮኖሚው ዋነኛ አምራች ሃይል እንዲሆኑ ማድረግ ለሀገር ጥቅሙ ትልቅ መሆኑን በማንሳት።

በአስተሳሰብ ረገድም ልዩነቶችንና ችግሮችን በሰላም ከመፍታት የተለየ አማራጭ እንደሌለ ያስተምራል ሲሉም ነው ዋና ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ የተናገሩት።

በመሆኑም የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ የአካባቢያቸው ተመልሰው ተቋቁመው በዘላቂነት የሰላምና የልማት ሃይል እንዲሆኑ ሁሉም አካል እገዛ ማድረግ አለበት ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top