በአማራ ክልል የፀጥታ ችግር የነበረባቸው አካባቢዎች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው ተመልሰዋል - አቶ ይርጋ ሲሳይ

2 Mons Ago
በአማራ ክልል የፀጥታ ችግር የነበረባቸው አካባቢዎች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው ተመልሰዋል - አቶ ይርጋ ሲሳይ

በአማራ ክልል የፀጥታ ችግሮች የነበሩባቸው አካባቢዎች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው ተመልሰው መደበኛ እንቅስቃሴዎች መቀጠላቸውን የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ገለፀ።

የብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በክልሉ ከወራት በፊት ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ በክልሉ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።

በርካታ አካባቢዎች ወደ ቀድሞ ሰላማቸው ተመልሰው መደበኛ እንቅስቃሴዎች መቀጠላቸውንም ጠቁመዋል።

የመንግስትን እና የፀጥታ መዋቅሩን በማጠናከር በተሟላ ቁመና ላይ እንዲገኝ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።

በተለይም የመንግስት አመራሩን በአራት ዙር በስልጠና በማሳተፍ የአመለካከት ዝንፈቶችን በማስተካከል አቅሙን እንዲገነባ ተደርጓልም ብለዋል።

ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሰላምን የማስፈን ስራ በስፋት መሰራቱን የጠቆሙት አቶ ይርጋ በዚህም መልካም ውጤቶች ታይተዋል ሲሉም ገልፀዋል። በተደጋጋሚ ከህብረተሰቡ ጋር በተደረጉ ውይይቶች የሰላም ፍላጎት ጎልቶ መታየቱንም አንስተዋል።

ችግሮችን በሰላም ለመፍታት መንግስት የሰላም ጥሪ በተደጋጋሚ እያቀረበ መሆኑን ተከትሎ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የተመለሱ ሀይሎች መኖራቸውንም አብራርተዋል። ሆኖም ግን አሁንም ቢሁን ሰላማዊ አማራጭን በማይከተሉ ሀይሎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ተደራጅቶ ፀጥታን እያስከበረ መሆኑም ተገልጿል።

የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብ እና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

በቀጣይም የመንግስት መዋቅሩን የበለጠ ለማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መንግስት በትኩረት ይሰራል ተብሏል። ነፃ የምርት ዝውውር እንዲኖርና በትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ እንዲቀጥል እንደሚደረግም ተጠቁሟል።

መሰረታዊ የሆኑ የህዝብ ጥያቄወችን በየደረጃው ለመመለስ የተግባር ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት አቶ ይርጋ፤ አሁን ላይ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ሂደቱን እያጓተቱ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በክልሉ የተከሰተው ድርቅ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊው ርብርብ እንደሚደረግም ገልፀዋል።

በይህነው ዋጋቸው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top