ድለላ በተግባር እና በሕግ ዓይን

7 Mons Ago
ድለላ በተግባር እና በሕግ ዓይን

አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በ1948 ዓ.ም በታተመው ‘መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ወሀዲስ’ መጽሐፋቸው ‘ደላላ’ የሚለውን ቃል ‘‘በቁሙ መደለል፣ ማታለል፣ መሸንገል” ይሉታል።

ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድህን ደግሞ በ1991 ዓ.ም ስለኢትዮጵያ የእህል ደላሎች ሚና ባቀረቡት የጥናት ጽሁፍ ላይ ‘ደላላ’ የሚለው ቃል ምንጩ አረብኛ መሆኑንን እና በሐገራችን ብቻ ሳይሆን በናይጄሪያ ‘ዲላላ’ በህንድ ‘ዳላል’ የሚለው ተመሳሳይ ስያሜ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ደላሎች ቤት ፤መሬት፣ መኪና፤ ማሻሻጥና ማከራየት ብቻ ሳይሆን ከምንመገበው እህል አንስቶ ሌሎች ቁሳቁሶችን፣ አሠሪና ሠራተኛ፣ የቤት ሠራተኛም ያገናኛሉ። በአምራቹ እና በጅምላ ወይም በችርቻሮ ሻጩ፣ በአጓጓዡ፣ በገዢና በሻጭ መሀከልም አይጠፉም። ሕገ ወጥ ደላሎች ከሕገ ወጥ ተግባራትና ከዋጋ መናር ጋር ብዙ ጊዜ አብረው ሲነሱም ይሰማል። በዛሬው የሕግ ጉዳይ ስለደላሎች ሕጋችን ምን እንደሚል እንመለከታለን።

ከተወሰኑት ልዩ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው የመድህን ድለላን የመሰሉ የውስን ግብይቶች ደላላነት በስተቀር በአብዛኛው የተለመደው የድለላ ተግባር እንደሌሎች ሥራዎች የተለየ የትምህርት ማስረጃ፣ ልምድ፣ የመነሻ እርሾ (ካፒታል)፣ ከስነ ምግባር እና ከብቃት አንጻር ማረጋገጫ ፈተና ስለማይጠይቅ እዚያው አካባቢያቸው ካለ መረጃ ተነስተው ወደ ድለላው የሚገቡ ብዙዎች ናቸው።

በየአካባቢያችን እንደምናስተውለው ከገዢ እና ከሻጭ የተሻለ መረጃ ባይኖራቸውም የቤት ኪራይም ሆነ ሽያጭ ዋጋ ወይም የሌሎች አገልግሎቶች ዋጋ የሚወሰነው በገበያው ወይም በሻጩ ሳይሆን በአካባቢው ደላሎች ነው። ይህን የገበያውን ሚና ደላሎች የሚወስኑት የሚያገኙትን አበል ለመጨመር ስለሚመቻቸው እና ዋጋ በጨመረ ቁጥር በመቶኛ የሚያገኙት ክፍያ ስለሚጨምር ነው። በአሁን ጊዜ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ከሞባይል ስልክ እስከ ቤት እንደልላለን የሚሉ ደላሎችን እያየን ነው። እግር እስኪነቃ ከመዞር ለደላሎችም ለተጠቃሚውም ይህኛው የተሻለ አማራጭ ይመስላል።

በ2013 ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣው የንግድ ሕጋችን አንቀጽ 54 ስለ ደላሎች እንዲህ ይላል:-

  1. ደላሎች ውል ተዋዋዮችን (እንደ ሽያጭ፣ ኪራይ፣ ኢንሹራንስ፣ የማመላለሻ ውል የመሳሰሉትን) የሚዋዋሉ ሰዎችን ፈልገው የሚያገናኙ እና የሚያዋውሉ፣ ድለላን ራሱን የቻለ የሙያ ተግባራቸው አድርገው ጥቅም ለማግኘት የሚሠሩ ሰዎች ወይም ይህንኑ የድለላ ሥራ የሚሠሩ የንግድ ማህበራት ናቸው። ብዙውን ጊዜ እንደምንታዘበው ግን ደላሎች ፈልገውን አያውቁም፤ ገዥ ወይም ሻጭ ነው ፈልጎ የሚያገኛቸው።
  1. ድለላ ጥቅም ለማግኘት የሚሰራ ራሱን የቻለ የሙያ ተግባር ሲሆን ደላላው ምንም ያገናኝ ምን በንግድ ሕጉ መሰረት ነጋዴ ነው፤ በመሆኑም የንግድ ፍቃድ ማውጣት አለበት።

የንግድ ፍቃድ ለማግኘት ደግሞ የድለላ ሙያ የሚጠይቀው ልምድ፣ የትምህርት ዝግጅት፣ አስፈላጊ ካፒታል፣ ቋሚ አድራሻ ያስፈልጋል። የንግድ ፍቃዱ በግል ንግድ ወይም በንግድ ማህበርነት የተመዘገበ መሆን አለበት። ስለዚህ እንደማንኛውም የንግድ ስራ ድለላ ከሚያስገኘው ገቢ ላይ ግብር ለማስገበር ያስገኘው ገቢና የሚከፍለው ግብር መታወቅ አለበት።

ተገቢው አካልም ትክክለኛውን አገልግሎት መስጠታቸውንና የግብር ግዴታቸውን መወጣታቸውን ለማረጋገጥ አሠራራቸውን ቁጥጥር ሊያደርግበት ይገባል። በተግባርስ? ሌላ ነው።ጥቂት የድለላ መስኮች ብቻ ናቸው በሕጋዊ መልኩ እየሠሩ ያሉት። የመድህን ዋስትና ደላሎች በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የሚሰጣቸው እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ናቸው።

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ቡና፣ ሰሊጥ እና ነጭ ቦለቄ የሚያገበያዩ ደላሎች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ፍቃድ አውጥተው አባል በመሆን ቁጥጥር እየተደረገባቸው ይሠራሉ።

ለዚህ አይነቶቹ የድለላ ሥራዎች ከፍተኛው የአገልግሎት ክፍያ በሚመለከተው ሕግ ተደንግጓል። ከአምራቹ እስከ ነጋዴው ያለው ረጅም የደላላ ቅብብሎሽ ሰንሰለት በማጠሩና ተገቢ ቁጥጥር የሚደረግበት ውድድር በመሀላቸው በመኖሩ የምርት ገበያው ደላሎች ኮሚሽን የሚያስከፍሉት በሕግ በተገደበ የመቶኛ ስሌት ነው ።

የቁም ከብት ግብይት ላይም በግብይቱ የመሐል ደላሎችን የሚቆጣጠር ተመሳሳይ አዋጅ ወጥቷል። ከእነዚህ ውጪ በተለይ በየሰፈራችን ያሉት የቤት ኪራይ እና ሽያጭ እና ሌሎችም ደላሎች ግን የተወሰኑት ካልሆኑ በስተቀር የንግድ ፈቃድ ያላቸውና ግብር የሚገብሩ አይደሉም።

አብዛኞቹ ሌሎች የተለመዱ የድለላ ሥራዎች ላይ ግን ፈቃዱን ለማግኘት ሙያው የሚያስፈልገውን መስፈርት የሚጠይቃቸው አካል ባለመኖሩ ልምድና ትምህርቱ እንዲሁም ስነ ምግባሩ የሌላቸው ደላሎችም ሲደልሉ ይታያል። በዚህም የተነሳ በተመጣጣኝ ዋጋ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ አገልግሎታቸውን እንዳናገኝ ሆነናል።

  1. የደላላ አበልን በተመለከተ የንግድ ሕጋችን "በደላላው አስማሚነት ውሉን ካስጨረሰ ወይም ካዋዋለ በኋላ የውሉ ግዴታ ቢፈፀምም ባይፈፀምም ደላላው አበሉ ይከፈለዋል" ይላል። በተግባር ግን የሚታየው ደላላው ዋጋ ይናገራል ቤቱን ወይም እቃውን ያሳያል ተከራክረው የሚያስማማቸው ዋጋ ላይ የሚደርሱት ግን ገዥና ሻጭ ወይም አከራይና ተከራይ ናቸው።
  1. ሕጉ እንደሚለው በልማድ የታወቀ ካልሆነ ወይም ሌላ ስምምነት ከሌለ ለደላላው አበል የሚከፍለው አገልግሎቱን የጠየቀው ሰው ብቻ ነው። በተግባር እንደምንታዘበው ግን ለአንድ አገልግሎት ደላላው ወይም ደላሎቹ ከሁለቱም ተዋዋዮች አበል ይቀበላሉ። ‘የሚከራይ ቤት አለኝ’ ብሎ አከራዩ ለደላላው ይናገራል። ደላላው ይህን መረጃ ይዞ ተከራይ አያፈላልግም ምን በወጣው! ተከራይ ራሱ ነው ‘ቤት እፈልጋለሁ’ ብሎ የሚመጣው። ሕጉ እንደሚለው ተዋዋዮችን ደላላው ስለማያፈላልግና አገልግሎቱን የሚጠይቁት ተዋዋዮች ስለሆኑ ደላላው ከሁለቱም አበል ይቀበላል።በተጨማሪም በአንድ ግብይት ውስጥ ከሁለቱም ተዋዋዮች በኩል ብዙ ደላሎች ስለሚኖሩ የግብይቱን ዋጋ እና የአበሉን መጠን በማናገር ገዢ ወይም ተከራይ ላይ ጫና ያሳድራል።
  1. የአበሉ መጠን በቅድሚያ በስምምነት መወሰን አለበት። ተዋዋዩ እና ደላላው የደለለበትን አበል ይህን ያህል እከፍላለው ብለው ቅድሚያ መስማማት አለባቸው ። በተግባር ግን ይህ ስምምነት በቅድሚያ ስለማይደረግ አብዛኛውን ጊዜ ደላላው ኪራይ ከሆነ የመጀመሪያውን ክፍያ 10 በመቶ ሽያጭ ከሆነ 2 በመቶ ይቀበላል።
  1. በንግድ ሕጉ መሰረት የድለላው አበል ላይ በቅድሚያ ስምምነት ካልተደረገ ሕጉ "የደላላው አበል በልማድ መሰረት ይቆረጣል" ይላል። በዚህ ምክንያት ይመስላል በአብዛኛው ደላሎች ቀድመው የአበላቸውን መጠን የማይጠይቁት። አበላቸውም በመቶኛ እንጂ በቁርጥ እንዲሆንም አይፈልጉም። ስለዚህ ለአንድ ቀን ቤቱን አሳይቶ ዋጋ ለተናገረበት ከላይ የጠቀስኩትን የልማድ ዋጋ የመቶኛ ስሌት በሁለቱም ተዋዋዮች በኩል ያሉት ደላሎች ያስከፍላሉ። ይህ የልማድ ዋጋ ለደላሎች ቢመችም ለተዋዋዮች እና ለሻጮች ግን በአብዛኛው ፍትሐዊ ወይም ከተሰጠው አገልግሎት ጋር ተመጣጣኝ አይደለም።
  1. ተዋዋዮ እና ደላላው የአበሉን መጠን ቢስማሙም እንኳን የተስማሙበት አበል ከባድ መስሎ ከታየው ወይም ደላላው ከሰጠው አገልግሎት ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑ ሲታየው የንግድ ሕጋችን በአንቀፅ 57 (3) ላይ ለፍ/ቤት የአበሉን መጠን የመቀነስ ስልጣን ሰጥቷል ። በተግባር ግን ደላሎች በዚህም በዚያም ብለው ተመጣጣኝ ሆነ አልሆነ የጠየቁትን ያስከፍላሉ።
  1. የንግድ ሕጉ አንቀፅ 57(4) ደላላው ኃላፊነት አለበት ይላል። ደላላው ለደንበኛው ወይም አገልግሎቱን ለጠየቀው ወገን ያሉበትን ግዴታዎች ተላልፎ የደንበኛውን ጥቅም በሚጎዳ አኳኀን ለሌላ 3ኛ ወገን ጥቅም የሠራ እንደሆነ ወይም ደንበኛው ሳያውቅ ከ3ኛ ወገን ክፍያ ከተቀበለ አበል የማግኘት መብቱ ቀሪ ይሆናል። በተግባር ግን ብዙዎች ደላላ ቢጎዳቸውም ከመበሳጨት በስተቀር በፍርድ ቤት ከሰው በኃላፊነት ካሳ ሲጠይቁ አይታይም።

ለማንኛውም ደላላ ስትጠቀሙ በተለይ አበሉን በተመለከተ በቁርጥ በቅድሚያ ተስማሙ። በመቶኛ ከሆነ አበላቸውን ለመጨመር ዋጋውን ከፍ ሊያደርጉት ስለሚችሉ በቁርጥ አድርጉት። አበሉን ተስማምታችሁም ቢሆን ከሰጡት አገልግሎት ጋር የክፍያው መጠን ከተጋነነ ይገባል ከምትሉት በላይ አልከፍልም በሉ። ጉዳዩ ፍ/ቤት ከደረሰ ሊቀነስላችሁ ይችላል። ቢቻል የንግድ ፍቃድ ባላቸው ደላሎች ተጠቀሙ። ደላላው የሚጠራውን ዋጋ ከማመናችሁ በፊትም በተለያየ ዘዴ የገበያውን ዋጋም ለማጣራት ሞክሩ።

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top